“የምርጫ ሂደታችንን ክብር የሚነካ አንዳች ነገር ሲፈጸም፣ እርምጃ መውሰዳችን የግድ መሆኑ፣ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም” ብለዋል የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ።
“በእርግጥም እናደርገዋለን” በማለት ሃሳባቸውን አጠናክረዋል፣ ሚስተር ኦባማ ዛሬ ጧት ኤንፒአር ለተባለው ራዲዮ በሰጡት ቃል።
አንዳንዶቹ እርምጃዎቻችን ግልፅና ሕዝብ የሚያውቃቸው ወይም የሚሰማቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ በተቃራኒ የሚወሰዱ እንደሚሆኑ ነው ፕሬዚዳንቱ ያስገነዘቡት።
የሩስያ የኢንተርኔት ሰርጎ ገቦች፣ በዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት፣ ከዲሞክራቲክ ፓርቲው ኮምፒተሮች ውስጥ፣ ስለ ሂለሪ ክሊንተን የምርጫ ዘመቻ አሳፋሪ የሆኑ ኢሜሎችን ይፋ እንዳደረጉ፣ ሲ አይ ኤ ድምዳሜ ላይ እንደደረሰ ማስታወቁ ይታወሳል።
ይህ ድርጊት ከሩስያው ፕሬዚደንት ከቭላዲሚር ፑቲን እውቅና ውጪ እንደማይሆን፣ የኋይት ሀውስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያምናሉ።
ሞስኮ ግን፣ ክሱን፣ አስቂኝና የማይረባ ትለዋለች።