የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዋይት ኃውስ ቤተ መንግሥት የግድግዳ ወለል ከቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ተርታ ለታሪክ የሚቀመጠውን የፎቶ ግራፍ ምስላቸውን ንድፍ በመግለጥ ይፋ የሚያደርጉትን የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና ቀዳማዊ እመቤት ሚሼል ኦባማን ተቀብለው እንደሚያስተናግዱ አስታወቁ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባለው ልማድ የአሁኑ ፕሬዚዳንቶች ፎቶ ግራፎቻቸውን የቤተ መንግሥቱ ክምሽት አካል አድርገው የሚያኖሩትን ከነሱ ቀድሞ የነበሩትን ፕሬዚዳንቶች ማስተናገዳቸው የተለመደ መሆኑን አሶሴትይድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ከፕሬዚዳንት ባይደን በፊት የነበሩት የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን ልማድ በራሳቸው የአስተዳደር ዘመን አልተከተሉም፡፡
በዚህም የተነሳ ባይደን በምክትል ፕሬዚዳንት ያገለገሏቸውን ፕሬዚዳንት ኦባማንና ባለቤታቸውን የፎቶግራፍ ንድፍ የማኖር ሥነ ስርዓት እንዲያካሄዱ መደረጋቸው ተመልክቷል፡፡
የዋይት ኃውስ ቤተ መንግሥት የመጀመሪያው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ከሆኑት ጆርጅ ዋሽንግተን ጀምሮ ያሉትን ፕሬዚዳንቶችና ቀዳማዊ እመቤቶች ፎቶግራፎችን በቅደም ተከተላቸው ደርድሮ ማስቀመጡ የተለመደ ነው፡፡
ፕሬዚዳንቶቹና ቀዳማዊ እመቤቶቹ ምስላቸውን በስዕል ቀርጾ የሚያስቀር የራሳቸውን አርቲስት የሚመርጡ መሆኑም ተመልክቷል፡፡