በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፕሬዝዳንት ኦባማ የኦርላንዶውን ጅምላ ግድያ በአሜሪካ ታሪክ “አሰቃቂው” ብለውታል


ፕሬዝዳንት ኦባማ
ፕሬዝዳንት ኦባማ

ዩናይትድ ስቴትስ ፕረዝዳንት ባራክ ኦባማ በኦርላንዶ-ፍሎሪዳ የተፈጸመውን ግድያ በማስመልከት ትላንት እሁድ በሰጡት መግለጫ “በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ አሰቃቂ ግድያ” ሲሉ አውግዘውታል። የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች የምሽት ከለብ ውስጥ የተፈጸመው ግድያ 50 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን ሌሎች ከ50 በላይ ማቁሰሉን ታውቋል። የከተማዋ ባለሥልጣናት ግድያው የሽብር ተግባር መኾኖን ለማጣራት ምርመራ ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ቅዳሜ ዕለት ለሊት በዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ፍሎሪዳ ከተማ ፐልስ በተባለው የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች የምሽት ክለብ ውስጥ የአፍጋኒስታ የዘር ሃረግ ያለው የ29 ዓመቱ አሜሪካዊ ኦመር ማቲን የደረሰውን የጅምላ ግድያ፤ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በአሜሪካና እሴቶቿ ላይ የተካሄደ ጥቃት ነው ብለውታል።

“ይህ ጥቃት የጥላቻና የሽብር ተግባር ነው። በአሁኑ ሰዓት ሁላችንም አሜሪካዊያን በአንድነት ሐዘን ላይ ነን። ዜጎቻችንንም ከእንዲህ አይነት አደጋ ለመከላከል መፍትሄ በማበጀትም ላይ ነን።” ብለዋል

ፕሬዝዳንት ኦባማ ጨምረው ሲናገሩ፤ እንዲህ አይነቱ አሰቃቂ ተግባር ሊፈጸምና እውን ሊኾን የቻለበት ዋናው ምክንያት በአሜሪካ መሳርያ ማግኘት በጣም ቀላል በመሆኑ ነው ካሉ በኋላ “እንደዚህ ዓይነት ሀገር ለመገንባት ፍላጎታችን መሆኑን መወሰን አለብን። በዚህ ጉዳይ ላይ ርምጃ አለመውሰድም ውሳኔ ነው።”ብለዋል።

ግድያውን የፈጸመው የ29 ዓመቱ ኦመር ማቲን የአፍጋኒስታ የዘር ሃረግ ያለው አሜሪካዊ ነው። በፍሎሪዳ ግዛት ኦርላንዶ ከተማ ፐልስ በተባለው የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች ክለብ ከለሊቱ ስምንት ሰዓት ገብቶ ውስጥ በነበሩ 300 ሰዎች ላይ ተኩስ መክፈቱን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

በክለቡ ውስጥ የነበሩት አንዳንድ ሰዎች በጀርባ በር በኩል ማምለጥ መቻላቸውን፣ ሌሎች ደግሞ ከታች በኩል ካለው የክለቡ ክፍል መሬት ላይ በመደበቅ ከተኩሱ ለማምለጥ መሞከራቸው ታውቋል። ከአደጋው የተረፈችው ሮዚ ፌቦ፤“መጀመርያ የሰማሁት ድምጽ ሙዚቃው ነበር የመሰለኝ ከዛ አየሁት። 20-30 ጫማ ርዝመት ያለው ሆኖ በያዘው መሳርያ ወደ ህዝቡ መተኮስ ጀመረ።ሁሉም ሰው ወደ መሬት ወደቀ።” በማለት ስለሁኔታው ትናገራለች።

ግድያውን የፈጸመው ግለሰብ በቦታ ከደረሱ የፖሊስ ሃይሎች ጋር በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ መሞቱንም ታውቋል። የፖሊስ ባለስልጣኖች ግለሰቡ ከአክራሪ የእስልምና እምንት ተከታዮች ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማረጋገጥ ምርመራ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በአሜሪካ የሚገኙ የእስልምና ኃይማኖት መሪዎች በበኩላቸው ድርጊቱን በመኮነን የዜና አውታሮች ግን ሁኔታው ከማባባስ ስሜታዊ ከሆነ ዘገባ እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውና ፈርስት ሂጂራ ፋውንዴሽን የተባለው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ድርጅት በበኩሉ ድርጊቱን አውግዞታል። የድርጀቱ መሪ አቶ ነጂብ መሐምድ ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ ሙስሊም ከመሆኑ ውጪ ከእስልምና ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ብለዋል።

ግድያውን የፈጸመው የ29 ዓመቱ ኦመር ማቲን አባት ሳዲቅ ማቲን በዚህ ቅዱስ በኾነው የሮሞዳን ፆም ወቅት ልጃቸው እንዲህ ያለ ድርጊት ሊፈጽም የቻለበት ምክንያት ግራ እንዳጋበቸው ተናግረዋል። ‘እኔ ለዚህ ምክንያቱ ምን እንደሆን አላውቅም። በልቡም ይህን ያህል ጥላቻ እንዳለ አላውቅም’ ብለዋል።

ይህን በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ አሰቃቂ የተባለውን የጅምላ ግድያ በርካታ የአሜሪካ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች እያወግዙት ይገኛሉ። የመጪው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እጩዎችም ድርጊቱን በማውገዝ ላይ ይገኛሉ።

ዝላቲካ ሆክ ያጠናቀረችውን ዘገባ አጣምራ ጽዮን ግርማ ይዛ ቀርባለች።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።

ፕሬዝዳንት ኦባማ የኦርላንዶውን ጅምላ ግድያ በአሜሪካ ታሪክ “አሰቃቂው” ብለውታል
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:46 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG