ትላንት ኀሙስ፣ ከዐዲስ አበባ ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ሲጓዙ የነበሩ 52 ሰዎች፣ በታጣቂዎች ታግተው እንደነበር የገለጸው በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር፣ ኾኖም አብዛኛዎቹ ወዲያውኑ አምልጠው ስምንት ተሳፋሪዎች ብቻ መቅረታቸውን አስታውቋል።።
በኦሮሚያ ክልል፣ በገብረ ጉራቻ እና ቱሉ ሚልኪ ከተሞች መካከል ባለ ቦታ ላይ፣ ከማሽላ ማሳ ውስጥ የወጡ ታጣቂዎች አውቶብሱን አስቁመው፣ አሽከርካሪውን ጨምሮ 52 ተሳፋሪዎችን ወደ ጫካ ወስደው እንደነበር ከእገታ ያመለጡ እማኞች ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደሪ አቶ ከፍያለው አደሬ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል፣ 52ቱ ተሳፋሪዎች፣ እርሳቸው “ሸኔ” ሲሉ በገለጹት ታጣቂ ቡድን ታግተው የነበሩ ቢኾንም፣ “የጸጥታ ኀይሎች ብዙዎቹን ማስለቀቅ ችለዋል፤” ብለዋል።
የቀሩትን ስምንት ተሳፋሪዎች ለማስለቀቅም “ጥረቱ ቀጥሏል” ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ድምፅ ባልደረቦች፣ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ምላሽ ለማግኘትና በዘገባው ለማካተት ጥረት አድርገዋል፤ ለጊዜው አልተሳካም።
ኾኖም ድርጅቱ፣ ከዚኽ ቀደም ለቀረቡበት መሰል ውንጀላዎች በሰጠው ምላሽ፣ ታጣቂዎቹ በእገታ ተግባራት ላይ እንደማይሳተፉ በመግለጽ በጽኑ አስተባብሏል።
መድረክ / ፎረም