በኮሪያ ልሣነ-ምድር ተፈጥሮ የነበረውን መቀራረብ ተከትሎ ፒዮንግያንግ ያፈራረሰቻቸውን የወሰን ኬላዎቿን ‘መልሳ እያጠባበቀች’ መሆኗን የደቡብ ኮሪያ ጦር ዛሬ አስታወቀ። ምክንያቱ ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ የወታደራዊ ስለላ ሳተላይት ማምጠቋን ተከትሎ በባላንጦቹ ጎረቤቶች መካከል ውጥረት እየተካረረ መምጣቱ መሆኑን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
በመሃከላቸው የነበረውን ፍጥጫ ለማርገብ የዛሬ አምስት ዓመት (በ2011 ዓ.ም.) ደርሰውበት በነበረ ስምምነት መሠረት ሁለቱም ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ ከሆነው ቀጣና ጋር በሚያዋስኗቸው መሥመሮች ላይ የነበሯቸውን እጅግ የተጠናከሩ 11 ኬላዎች አፍርሰው ወታደራዊ ግጭቶችን ለማርገብ ወስነው እንደነበር ኤፒ በዘገባው አስታውሶ አሁን ግን ውሉን ሊጥሱ እንደሚችሉ ሁለቱም እየዛቱ መሆናቸውን አመልክቷል።
ሁለቱ ኮሪያዎች የአየር ስለላዎችን ለማቆምና ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ ከሆነው ቀጣና ጋር ተዋሳኝ በሆኑ የፈሪ ወረዳዎቻቸው ውስጥ በመሣሪያ ተኩስ የታጀቡ ወታደራዊ ልምምዶችን ላለማድረግ፣ እንዲሁም ግንባር መሥመር ከነበሩት የጥበቃ ኬላዎች የተወሰኑትን ለማንሣትና የተቀበሩ ፈንጂዎችን ለማውጣትና ለማስወገድ ተስማምተው እንደነበር የዜና አውታሩ አክሎ አስታውሷል።
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ማክሰኞ (ኅዳር 11) ለመጀመሪያ ጊዜ ለወታደራዊ የስለላ ጉዳይ አውለዋለሁ ያለችውን ሳተላይት ማምጠቋን ካወጀች ወዲህ ደቡብ ኮሪያም ስምምነቱን በከፊል አቋርጣ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ በሆነው ቀጣና ተዋሳኝ መሥመር ላይ ቀደም ሲል የነበራትን የአየር ቅኝት እንደገና እንደምትጀምር አስታውቃለች።
ሶል እንቅስቃሴዋን “ለሰሜን ኮሪያ ደቡብ ጎረቤቷ ለመሰለልና የሚሳይል ቴክኖሎጂዋን ለማሳለጥ ስትል ፈፅማዋለች” ላለችው አድራጎት “እጅግ አነስተኛ የአፀፋና እራስን የመከላከል እርምጃ” እንደሆነ ማሳወቋን አሶሲየትድ ፕሬስ አክሎ ጠቁሟል።
መድረክ / ፎረም