በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችው አህጉር አቋራጭ ሚሳይል ከጃፓን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ክልል ውስጥ አረፈ


የሰሜን ኮሪያ የተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ የሚያሳይ የዜና ሽፋን በሴኡል፣ ደቡብ ኮሪያ
የሰሜን ኮሪያ የተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ የሚያሳይ የዜና ሽፋን በሴኡል፣ ደቡብ ኮሪያ

ለዩናይትድ ስቴትስ እና ለሸሪኮቿ የተጠናከረ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምላሽ ብርቱ የአጻፋ እርምጃ እንደምትወስድ ባስጠነቀቀሽ ማግስት ሰሜን ኮሪያ ዛሬ አርብ የአህጉር አቋራጭ የተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ አደረገች። የሚሳይል ሙከራው የዩናይትድ ስቴትስ እና ጃፓን የጋራ የአየር ኃይል ጦር ሠፈርን ከለላ ፍለጋ እንዲጠጉ ያስገደደ ነበር።

የጃፓን ባለሥልጣናት እንደገለጡት የሰሜን ኮሪያው አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤል /ICBM/ በጃፓን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ ከማረፉ በፊት ከአንድ ሰዓት በላይ አየር ላይ ሲምዘገዘግ ቆይቷል። ከሰሜናዊ ጃፓኗ የሆካይዶ ደሴት ግዛት በስተምዕራብ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ባሕር ላይ ነው ያረፈው።

በሰሜናዊ ሆንሹ ደሴት የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ እና የጃፓን የጋራ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ሚሳዋ በፌስቡክ ገፁ እንዳሰፈረው ባለሥልጣናቱ የሰሜን ኮሪያውን የሚሳኤል ሙከራ ሳይጠቅሱ ለጥንቃቄ ሲባል በጦር ካምፑ ያሉ ከለላ እንዲይዙ የሚጠይቅ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል ሰሜን ኮሪያ ላስወነጭፈችው የሚሳይል ሙከራ ምላሽ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሯ ደቡብ ኮሪያ በሌዘር ብርሃን እየተመሩ ኢላማቸውን የሚመቱ ኤፍ-35A ተዋጊ ጄቶችን ያካተቱ የጋራ የአየር ልምምዶችን አድርገዋል ሲል የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ዋሽንግተን ላይም የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደህንነት መሥሪያ ቤት “የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በመጣስ ሳያስፈልግ ውጥረት እንዲያይል የሚያደርግ እና በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ የሚያውክ አደጋ ደቃኝ ነው” ሲል የሰሜን ኮሪያን የሚሳይል ሙከራ አውግዟል።

የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ኃይልም በበኩሉ ድንገቱ በኮሪያ እና በአጠቃላይ በአካባቢው "ሠላምና መረጋጋትን የሚያውክ ብርቱ ትንኮሳ እና ከባድ ሥጋት ደቃኝ ነው” ብሏል።

አገራቸው የሰሜን ኮሪያን ድርጊት አስመልክቶ “ጠንካራ ተቃውሞ” ማስመዝገቧን የተናገሩት የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳም ይህም “ጠብ አጫሪ ትንኮሳዋ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተደጋግሟል። እነዚህን ድርጊቶች በፍጹም ልንታገስ አንችልም።” ሲሉ በክልላዊው ጉባኤ እየተሳተፉ ካሉበት ታይላንድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ሚሳይሉ ከዩናይትድ ስቴትስ ግዛት መድረስ የሚችል ነው ያሉት የጃፓኑ የመከላከያ ሚኒስትር ያሱካዙ ሃማዳ፡ አክለውም 15,000 ኪሎ ሜትሮች መወንጨፍ የሚችል መሆኑን አስረድተዋል።

በሶል በሚገኘው የኢውሃ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ሌፍ ኤሪክ ኢስሊ እንደሚሉት የሚሳይል ሙከራው “ፒዮንግያንግ ወታደራዊ ውጥረትን በማባባስ እና ከዩናይትድ ስቴትስን ከተሞች መድረስ የሚችል የኒውክሌር ጥቃት የማድረግ አቅም እንዳላት በማሳየት የሚደረግባትን ዓለም አቀፍ ጫና ለማደናቀፍ እየሞከረች ነው።” ብለዋል።

ሰሜን ኮሪያ ያስፈነጨፈቻቸው አገር አቋራጭ የቦለስቲክ ሚሳይሎችን አታለች። ተንታኞች እንደሚሉት፡ ሚሳኤሎቹ ብቃታቸውን የሚያረጋግጡትን የቴክኒክ መስፈርቶችን እንዲያሟሉ፣ ወደ ከባቢ አየር ዘልቆ ከመግባት መትረፍን ጨምሮ ቀጣይ ሙከራዎችን ይጠይቃል።

ያሁኑ የሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ ዜና የመጣው በርካታ የዓለም መሪዎች ለእስያ-ፓስፊክ የምጣኔ ሃብት ትብብር ጉባኤ ኤፔክ ታይላንድ ላይ በተሰበሰቡበት ወቅት ነው።

በኤፔኩ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የዩናይትድ ስቴትስን ልዑካን የመሩት ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ የደቡብ ኮሪያን፣ የጃፓንን፣ የአውስትራሊያን፣ የካናዳን እና የኒውዚላንድን መሪዎች ያካተተ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።

መሪዎቹ “የአካባቢውን ደህንነት የሚያናጋ እና አላስፈላጊ ውጥረቶችን የሚፈጥር” የሰሜን ኮርያን ድርጊት በጽኑ ማውገዛቸውን ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG