ዩናይትድ ስቴትስ የአጋሮቿን የደቡብ ኮሪያን እና ጃፓንን ደህንነት ለማጠንከር ያላትን ቁርጠኝነት መግለጿን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ ጠንካራ ወታደራዊ ምላሽ እንድምትሰጥ ካስጠነቀቀች በኋላ ዛሬ ሀሙስ የአጭር ርቀት የባለስቲክ ሚሳዬል ለሙከራ ወደ ምስራቅ የባህሯ ክፍል አቅጣጫ ማስወንጨፏን አስታውቃለች።
በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከጧቱ 10:48 ላይ ከሰሜን ኮሪያ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ የተተኮሰው ሚሳዬል በኮሪያና ጃፓን መካከል በሚገኘው ባህር ላይ ማረፉን አጎራባቾችዋ አገሮች አስታውቀዋል።
ሰሜን ኮሪያ በቅርብ ወራት ውስጥ ለሙከራ ካስወነጨፈቻቸው በርካታ ሚሳዬሎች ይህኛው የቅርብ ጊዜው ሲሆን፣ በስምንት ቀናት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተኮሰቸው ባለስቲክ ሚሳዬል መሆኑ ተመልክቷል።
አንዳንዶቹ ሙከራዎች በደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ስቴትስን ዒላማ ያደረጉ የኒዩክለር ጥቃቶች የአብነት ልምምዶች መሆናቸውን ሰሜን ኮሪያ ቀደም ሲል ማስታወቋ ተመልክቷል።
ብዙ ባለሙያዎች ሰሜን ኮሪያ ውሎ አድሮ የተቃናቃኞችዋን ትልቅ የመደራደሪያ አቅም ለመንጠቅ ስትል የኒዩክለር አቅሟን ማሳደግ ትፈልጋለች ማለታቸውን የአሶሴትይድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል።