የኬንያ ብሄራዊ አየር መንገድ (ኬኒያ ኤየርዌይስ) አብራሪዎች የሥራ ማቆም አድማ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መገታቱን ተከትሎ ትናንት ረቡዕ አየር መንገዱ መደበኛ ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ለአራት ቀናት በዘለቀው የአብራሪዎች አድማ የተነሳ ከአፍሪካ ትላልቅ አየር መንገዶች አንዱ የሆነው የኬንያ ኤርዌይስ በርካታ በረራዎች መሰረዝ መሰረዝ እና የብዙ ሺህ መንገደኞች ጉዞ ተስተጓጉሏል፡፡
የአብራሪዎቹ ማኅበር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በናይሮቢ ጆሞ ኬኒያታ የአይሮፕላን ጣቢያ የሥራ ማቆም አድማውን ያካሄደው ጡረታን አና የቆዩ ክፍያዎችን በሚመለከቱ ጭቅጭቆች የተነሳ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
የሥራ ማቆም አድማው በአየር መንገዱ ላይ ወደ 12 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ ማስከተሉ ተገልጿል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በበኩላቸው ኪሳራው ከተባለውም በላይ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
የአሠሪ እና ሠራተኛ ግንኙነት ዳኛ አን ሟሬ አብራሪዎቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ከትናንት በስተያ ማክሰኞ ነው ትዕዛዝ የሰጡት፡፡