በአፍሪካ የሳህል ቀጠና ውስጥ ጽንፈኛ እና አክራሪ ቡድኖችን ለመዋጋት የሚደረገው ወታደራዊ ጥረት ወሳኝ የአፍሪካ አገራት ከሆኑት ኒጀር እና ቻድ፣ የአሜሪካ ወታደሮችን ለማስወጣት የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አለመደረሱን አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ባለሥልጣን ለአሶሼትድ ፕሬስ ረቡዕ እለት ተናግረዋል።
ኒጀርን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግስት፣ የአሜሪካ ወታደሮች በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችለውን ስምምነት ባለፈው ወር አቋርጧል። በጎረቤት የምትገኘው የቻድ መንግሥትም፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ ባለው ስምምነት ላይ ጥያቄ ማንሳቱን፣ የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ክርስቶፈር ግሬዲ በቅርቡ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ የነበራት ስምምነት፣ አሜሪካ በእነዚህ ሀገራት ድንበሮች ውስጥ ወሳኝ የፀረ-ሽብር ተግባራትን ለማካሄድ የሚያስችላት ሲሆን፣ በሁለቱም አገራት ውስጥ የሚገኙ አጋር ወታደሮችን አሰልጥናለች።
ግንኙነቱን ለማቋረጥ የተደረገው ውሳኔ ዩናይትድ ስቴትስ በአፍሪካ ላይ የነበራት ተፅእኖ በሩሲያ እና በቻይና እየተቀለበሰ መሆኑን ያሳያል የሚስል ስጋት ፈጥሯል።
"ሁላችንም አጋር የምንሆነው በምርጫ መሆኑን ለማሳየት እየሞከርን ነው" ያሉት ግሬዲ "ከእነሱ ጋር ያለን አጋርነት ለምን አስፈላጊ ነው ብለን እንደምናምን የመወሰኑ ኃላፊነት የኛ ነው። በእርግጥ በዛ መኖር እንፈልጋለን። ልንረዳቸው፣ ልናሰለጥናቸው እንፈልጋለን። ነገሮችን በእነሱ በኩል፣ ከእነሱ ጋር ለእነሱ መስራት እንፈልጋለን" ብለዋል
የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ቅዳሜ እለት ጦሩን ከኒጀር ማስወጣት እንደሚጀምር ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ አዲስ ወታደራዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ ንግግር ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ሁለቱም አገራት ዩናይትድ ስቴትስ እዚያ መቆየት እንደማትችል ከወሰኑ፣ የአሜሪካ ወታደሮች በሳህል ዙሪያ የጸረ-ሽብር ተልእኮዎችን ለማካሄድ ሌሎች አማራጮችን መፈለግ እንዳለባቸው ግሬዲ ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም