በሰሜን ኮሪያ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ አትኩረው የሚሠሩ ቡድኖች ከዩናይትድ ስቴትስ የሚሰጣቸው የገንዘብ ድጋፍ መቋረጡ የተነገራቸው ሲሆን በዚህም የተነሳ የህልውና አደጋ እንደተደቀነባቸው ተነገረ፡፡ ይህንን ያስታወቁት በአብዛኛው በደቡብ ኮሪያ ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ምንጮች ናቸው፡፡
የአሜሪካ ድምጽ በተመለከታቸው ሰነዶች መሠረት ለተቋማቱ አብዛኛውን የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጡት በዓለም ዙሪያ የዲሞክራሲያዊ ተቋማት ለማጠናከር በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የተቋቋመው ናሺናል ኢንዳውመንት ፎር ዲሞክራሲ በምህጻር ኔድ እና የዩናይትድ ስቴትስ የዲሞክራሲ የሰብአዊ መብቶች እና የሠራተኞች ጉዳይ ክፍል ሲኾኑ ድጋፉ መቋረጡን ባለፉት ሳምንታት አሳውቀዋቸዋል፡፡
የገንዘብ ድጋፉ መቋረጥ ፊቱንም ጠንካራ ያልሆኑትን የሰሜን ኮሪያ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የባሰ በማዳከም ከዓለም እጅግ ዝግ እና በአፋኝ መንግሥታት ከሚገዙ ሀገሮች አንዷ በሆነችው ሀገር ለምርምር እና ለመብት ተሟጋች ሥራዎች ወሳኝ የሆኑ ምንጮች እንዲጠፉ ሊያደርግ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
የገንዘብ ድጋፉ መቋረጥ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ የፌደራል መንግሥቱን ቢሮክራሲ ለማስተካከል ብሎም ከግብር ከፋዮች የሚሰበሰበው ገንዘብ አወጣጥ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" ከሚለው አጀንዳቸው ጋራ እንዲቀናጅ ለማድረግ ከባለብዙ ቢሊዮን ባለሀብቱ ኢላን መስክ ጋራ ሆነው የያዙት ርምጃ አካል ነው፡፡
ኢላን መስክ ኔድ፣ ናሽናል ኢንዳውመንት ፎር ዲሞክራሲ ተቋምን "አጭበርባሪ እና እጅግ መጥፎ ድርጅት በመኾኑ መፍረስ አለበት" በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
መድረክ / ፎረም