ዋሺንግተን ዲሲ —
የቦርኖ ክፍለ ሃገር ፖሊስ ቃል አቀባይ ኢሱኩ ሰለጉዳቱ ሲናገሩ ማዱጉሪ ከተማ ከሚገኘው የፌዴራሉ ፍርድ ቤት ፊትለፊት ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ወደ ፍተሻ ኬላው ሲንደረደሩ፥ ፖሊስ እርምጃ ለመውሰድ ተገድዷል ብለዋል።
አንደኛዋ አጥፍቶ ጠፊ ሴት የታጠቀችውን ፈንጂ ለኩሳ እራሷንና አንደኛውን ግብረአበሯን መግደሏንም አስረድተዋል። ሁለተኛዋ አጥፍቶ ጠፊ ግን በቁጥጥር ሥር ውላ በምርመራ ላይ እንደምትገኝ ተገልጿል።
በባለሥልጣናቱ ተጨማሪ መግለጫ ከዚሁ ከተማ ወጣ ብሎ ሌሎች ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች በአንድ የአውቶቡስና ታክሲ መናኸሪያ ሥፍራ ላይ ጥቃት አድርሰው እራሳቸውንና ሁለት የሲቪል ተከላካይ ተዋጊዎችን ገድለዋል።
በናይጄሪያ አጥፍቶ ጠፊዎች ባለፉት ሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ጥቃት ሲያደርሱ የዛሬው አምስተኛ ሲሆን አካባቢው ከ20 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለው፣ የሀገር በቀሉ ሙስሊም ነውጠኛ ቡድን የቦኮ ሃራም ትውልድ ሥፍራ መሆኑ ይታወቃል።