በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በናይጄሪያ ጎርፍ ባስከተለው አደጋ ከ300 በላይ ሰዎች ሞቱ


በናይጄሪያ ጎርፍ
በናይጄሪያ ጎርፍ

ናይጄሪያ ከአስር ዓመታት ወዲህ አይታ በማታውቀው ጎርፍ በመመታት ላይ መሆኗንና በዚህ ዓመት ከ300 በላይ ዜጎቿ እንደሞቱባት አሶስዬትድ ፕረስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በዚህ ሳምንት ብቻ 20 ሰዎች በጎርፍ መወሰዳቸውንና አደጋው ሀገሪቱ መቆጣጠር ከምትችለው በላይ መሆኑ ተነግሯል።

ጎርፉ በናይጄሪያ ካሉ 36 ግዛቶችና ከተማዎች ውስጥ 27ቱን ሲያጥለቀልቅ ወደ መቶ ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎችን አፈናቅሏል። አምስት መቶ የሚሆኑ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል የሀገሪቱ ብሔራዊ የድንገተኛ አደጋዎች መክላከያ ቢሮ አስታውቋል።

አደጋው በሺዎች ሄክታር የሚቆጠር የእርሻ መሬት እንዳጠፋና ይህም በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ቀዳሚ በሆነችው ሀገር የምግብ አቅርቦት ችግርን እንዳይፈጥር ተሰግቷል። በሀገሪቱ ሰሜን ምዕራብና ማዕከላዊ ክፍል ያለው ግጭት ወትሮውንም የምግብ አቅርቦቱን አስቸጋሪ አድርጎታል።

የአካባቢ ጥበቃ መመሪያዎችን ባለመከተልና በቂ የሆነ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ናይጄሪያ በየዓመቱ በጎርፍ ትጠቃለች። በዚህ ዓመት የደረሰው ጐርፍ ግን በአካባቢ ወንዞች መሙላት፣ ያልተለመደ የዝናብ መጠንና በካሜሩን ከሚገኘው ላድጎ ግድብ በሚመጣ ተረፈ ውሃ አማካኝነት እንደሆነ ባለስልጣናት የናገራሉ።

በሀገሪቱ ከሚገኙ ግድቦች ሁለቱ ሞልተው መፍሰስ በመጀመራቸው በሚቀጥሉት ሳምንታት ችግሩ ሊባባስ እንደሚችል የሀገሪቱ ብሔራዊ የድንገተኛ አደጋዎች መክላከያ ቢሮ አስጠንቅቋል።

XS
SM
MD
LG