የሃይማኖታዊ ጽንፈኞችን ተደጋጋሚ ጥቃቶች ለመከላከል እየታገለ እንደሚገኝ የሚገልጸው 29 የኒጀር ወታደራዊ ሁንታ፣ አገሪቱ ከማሊ በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ ወታደሮቹ እንደተገደሉበት አስታወቀ።
“ቁጥራቸው ከ100 በላይ የሚደርሱ ጽንፈኞች፣ በድንበር አካባቢ በተሰማሩ የጸጥታ ኀይሎች ላይ ባነጣጠሩት ጥቃታቸው፣ ጓዳ ሠራሽ ፈንጂዎችን ተጠቅመዋል፤” ሲሉ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሌተናል ጀነራል ሳሊፉ ሞዲ፣ ትላንት ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። በኒጀር ወታደሮች ላይ ይህን መሰል ጥቃት ሲፈጸም፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ መኾኑ ነው።
የኒጀር ጦር ሥልጣኑን በተቆጣጠረበት በመጀመሪያው ወር፣ ከጽንፈኞች ጥቃት ጋራ የተያያዘ ሁከት፣ ከ40 በመቶ በላይ እንደጨመረ፣ በዓለም ዙሪያ የትጥቅ ግጭቶችንና ቀውሶችን የሚያጠና ቡድን ገልጿል። ባለፈው ነሐሴ ወር የታየውና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የታለመው የሃይማኖታዊ ጽንፈኞች ጥቃት፣ በቀደመው ወር ከተመዘገበው ጋራ ሲነጻጸር በአራት ዕጥፍ አሻቅቧል፡፡ በቲላበሪ ግዛት ውስጥ፣ በጸጥታ ኀይሎች ላይ በተሰነዘረ ጥቃት 40 ያህል ወታደሮች እንደተገደሉ፣ የጥናት ፕሮጀክቱ አክሎ አመልክቷል።
ጥቃቱ፣ “ለበርካታ ጀግና ወታደሮቻችንን አሳዛኝ አሟሟት ምክንያት ኾኗል፤” ሲሉ፣ በትላንቱ መግለጫቸው ይፋ ያደረጉት ጀነራል ሞዲ፣ ኹኔታውን እንደገመገሙት ጠቅሰው የጥናት ውጤቱንም ዘርዝረዋል፡፡ “በወገን በኩል 29 ወታደሮች ወድቀዋል። በአንጻሩ ከጠላት ወገን በርካታ አሸባሪዎች ሲገደሉ፣ 15 ሞተር ሳይክሎቻቸው ወድመዋል፤ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሣሪያ እና ጥይት ተይዟል፤” ብለዋል ጀነራል መኰንኑ።
ይህንም ተከትሎ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን የአገሪቱን መንግሥት፣ ባለፈው የሐምሌ ወር በመፈንቅለ መንግሥት አስወግዶ ሥልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ሁንታ፣ ለሦስት ቀናት ብሔራዊ ኀዘን ዐውጇል።
መድረክ / ፎረም