በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኒዤራውያን ሠራዊቱን የሚያጠናክር የበጎ ፈቃደኞች ምልመላ እንዲደረግ ጥሪ እያቀረቡ ናቸው


በኒዤር ጁንታ ደጋፊዎች የፈረንሳይ ኤምባሲ ደጃፍ ተሰብስበው፤ ኒያሜ፣ ኒዥር
በኒዤር ጁንታ ደጋፊዎች የፈረንሳይ ኤምባሲ ደጃፍ ተሰብስበው፤ ኒያሜ፣ ኒዥር

የምዕራብ አፍሪካ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ(ኤኮዋስ) ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያሰጋቸው በኒያሜ ያሉ ኒዤራውያን ነዋሪዎች፣ ብሔራዊውን ሠራዊት የሚያጠናክር የበጎ ፈቃደኞች የድጋፍ ምልመላ እንዲደረግ ጥሪ አድርገዋል።

በኒዤር፣ ወታደራዊ ሁንታው፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዙምን፣ ከሦስት ሳምንት በፊት ከሥልጣን ከአስወገደና በሀገር ክሕደት እንደሚከሥ ከአስታወቀ በኋላ፣ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣናቸው እንዲመልሳቸው ቀነ ገደብ ያስቀመጠው ኤኮዋስ፣ ወታደራዊ ጣልቃ ገብ ርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ሁንታው ድጋፍ የሚያስፈልገው ከኾነ፣ በ10ሺሕ የሚቆጠሩ በጎ ፈቃደኞች፣ በውጊያም ይኹን በሕክምና፣ እንዲሁም በአቅርቦት አገልግሎት ውስጥ ለመሳተፍ ምልመላ እንዲደረግ፣ የዋና ከተማዋ ነዋሪዎች ጥሪ በማድረግ ላይ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሁንታው፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ የሾማቸው ዓሊ ማሐማን ላሚን ዘይን፣ በጎረቤት ቻድ ድንገተኛ ጉብኝት አድርገዋል።

የኤኮዋስ ወታደራዊ አዛዦች፣ ነገ ኀሙስ እና ከነገ በስቲያ ዐርብ፣ በጋና ተሰብስበው፣ በኒዤር ወታደራዊ ጣልቃ ገብ ርምጃ በሚወስዱበት ኹኔታ ላይ ይነጋገራሉ፤ ተብሏል።

ተንታኞች እንደሚያመላክቱት ግን፣ ከኤኮዋስ የውስጥ ክፍፍል እና ከቀጣናው አለመረጋጋት አንጻር፣ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቱ፣ በተግባራዊነቱም ኾነ በፖለቲካዊ ዐይን አደገኛ ውጤት ይኖረዋል።

በሌላ በኩል፣ በጂሃዲስች የተፈጸመ ነው በተባለ የደፈጣ ጥቃት፣ 17 ወታደሮቹ እንደተገደሉ፣ ሁንታው አስታውቋል። 20 ተጨማሪ ወታደሮች እንደተጎዱና ከእኒኽም ውስጥ ስድስቱ፣ በአስጊ ኹኔታ ላይ እንደሚገኙ፣ የመከላከያ ሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል።

ጥቃቱን ፈጽመዋል የተባሉና በሞተር ብስክሌት ሲጓዙ በነበሩ ከ100 በላይ ነውጠኞች ላይ፣ ርምጃ መወሰዱን፣ የመከላከያ ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG