የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሔሊን አውሎንፋስ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ለመጎብኘት ዛሬ ሐሙስ ወደ ፍሎሪዳ እና ጆርጂያ ግዛቶች እንደሚያመሩ ተገለጠ። በአደጋው ምላሽ ጥረቶች ላይ ከተሳተፉ የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪዎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት ጋርም ይገናኛሉ።
ረቡዕ እለት ባይደን የሰሜን እና ደቡብ ካሮላይና ግዛቶችን የጎበኙ ሲሆን፣ ሔሊን በሰሜን ካሮላይና ያደረሰውን ጉዳት በሄሊኮፕተር ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኃላ "አውሎንፋሱ ያደረሰውን ጉዳት ለመጠገን እና የተጎዱ ማህበረሰቦችን መልሶ ለማቋቋም በቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላር ይጠይቃል" ብለዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ኻሪስም ትላንት ረቡዕ በጆርጂያ ክፍለ ግዛት ተመሳሳይ ላይ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ በቀይ መስቀል ማዕከል ተገኝተው ሔሊን አውሎንፋስ ያደረሰችውን ጉዳት ተከትሎ አካባቢው ያለበትን ሁኔታ የተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
"በዚህ አውሎንፋስ እና ባስከተለው ቀውስ ሳቢያ ብርቱ ጉዳት እና አሰቃቂ ስሜት ተፈጥሯል" ያሉት ኻሪስ "ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት በሚደረገው ጥረት አብረናችሁ ነን" የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ባይደን ሔሊን አውሎንፋስ ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች የሚደሰጠውን ድጋፍ ለማገዝ 1 ሺህ ወታደሮች እንዲሰማሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
መድረክ / ፎረም