በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኒው ዚላድ ውስጥ የኮቪድ ክትባት ግዴታና ገደቦች በመቃወም ነዋሪዎች ሰልፍ ወጡ


ተቃዋሚዎች በዌሊንግተን የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ
ተቃዋሚዎች በዌሊንግተን የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ

ኒው ዚላንድ ውስጥ ተቃዋሚዎች የኮቪድ ክትባት ግዴታ መደረጉ እና የእንቅስቃሴ ገደቦችን በመቃወም ሰልፍ አደረጉ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሰልፈኞቹ አብዛኛውን የሀገሪቱን ህዝብ አይወክሉም ብለዋል።

በዋና ከተማዋ ዌሊንግተን በሚገኘው የሀገሪቱ ፓርላማ ደጃፍ የተሰበሰቡት በብዙ ሺዎች የተቆጠሩ ተቃዋሚዎች መንግሥት ኮቪድ-19 ለመከላከል ያወጣቸው የእንቅስቃሴ ገደቦችን እና ክትባት መከተብ ግዴታ መደረጉን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።

ቁጥራቸው ወደ 3000 የተገመቱት ተቃዋሚዎች የእንቅስቃሴ ገደቦቹን የሚያወግዙ እና የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የምርጫ ዘመቻ ባንዲራዎች አንግበው ከተማዋ ውስጥ ሰልፍ አድርገዋል፤ የጸጥታ ሃይሎች የምክር ቤት ህንጻው መግቢያ በሮችን አጥረዋል።

የኒው ዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደርን በፓርላማው ውስጥ ሆነው ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል "ዛሬ ያየነው የሚበዛውን ህዝብ የሚወክል አይደለም” ብለዋል። አምስት ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኒው ዚላንድ ኮቪድ-19ን በከፍተኛ ደረጃ ከተቆጣጠሩ ሀገሪች መካከል አንዷ ነች፤ ኮቭድ-19ን ለማስወገድ የተጠቀመችበት መንገድ በአብዛኛው የተዋጣላት ሲሆን ዓለም አቀፉ ወረርሲኝ ከተከሰተበት ጊዜ ወዲህ በጠቅላላው በበሽታው ምክንያት የሞቱባት ሃያ ስምንት ሰዎች ብቻ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሲንጋፖር ባለሥልጣናት እአአ ከታህሳስ ስምንት ቀን ጀምሮ በራሱ ምርጫ የኮቪድ-19 ክትባት ያልተከተበ ሰው ኮቪድ-19 ቢታመም የህክምና ወጪውን መንግሥት የማይከፍልለት መሆኑን የሃገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

አሁን ባለው አሰራር የሀገሪቱ ዜጎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እና የረጅም ጊዜ ቪዛ ያላቸው ሰዎች በኮቪድ-19 ቢታመሙ የህክምና ወጪያቸውን ይሸፍናል፤ ይህ ግን ከሀገር ውጭ ተጉዘው እንደተመለሱ የታመሙ ሰዎችን አይጨምርም።

ሰማኒያ አምስት ከመቶው የሲንጋፖር ህዝብ የኮቪድ ክትባት ተከትቧል። ሆኖም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመመጣቱ የሀገሪቱን የጤና ጥበቃ ስርዓት ከአቅም በላይ ያጨናንቃል የሚል ስጋት መኖሩ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG