በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

2019


ዓለም አዲሱን የአውሮፓ 2019 ዓ.ም. ስታስተናግድ ዋናና ትላልቅ ከተሞች ደምቀው አንግተዋል።

ዓለም አዲሱን የአውሮፓ 2019 ዓ.ም. ስታስተናግድ ዋናና ትላልቅ ከተሞች ደምቀው አንግተዋል።

ከናቫሲቢርስክ እስከ ሃዋኢ በተዘረጋችው ዓለም፣ ከዌሊንግተን እስከ ሆኖሉሉ ባሉ የጊዜ ቀጣናዎች ስለአዲሱ 2019 ዓ.ም. ብሥራት የተዘሩ የርችት እንቁጥቁጦች የዕኩለ-ሌሊቱን ሰማዮች በብርሃንና በብዙ ድምፅ በየሰዓቱ ሲቀድዱ ሙሉውን አዲስ ቀን ደፍነውታል። ብዙ መዝሙር፣ ብዙ ዘፈን፣ ብዙ ጭፈራ፣ ብዙ ምሥጋና፣ ብዙ ምኞት በዚህች ክፉ በዝቶ በሚውልባት፤ ተስፋ ግን ጨርሶ ባልራቃት ዓለም ዙሪያ ብዙ ተስፋ ሲዘንብ አድሮ ሲዘንብ ውሏል።

በሺኾችና በሺኾች የተቆጠሩ የአዲሱ ዓመት ጠባቂዎች የኒው ዮርኩን ታይምስ አደባባይ እስከገደፉ ሞልተውት የአሮጌውን ዓመት የመጨረሻ ሽርፍራፊ ጊዜ ለማሰናበት ሲቆጥሩ የኒውዚላንዷ ዊሊንግተን ላይ ቀኑ አርጅቶ ተስያት አሥር ሰዓት ሆኖ ነበር። ሲድኒ ላይ ዘጠኝ፣ ቶኪዮ ላይ ስምንት፤ አዲስ አበባ ላይ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ... በኢትዮጵያና በቀሪው ዓለም የጊዜ ቀመርም ልዩነቱ ከሰባት ዓመት ወደ ስምንት ዓመት አሻቀበ -- ኢትዮጵያ ሂዱና በስምንት ዓመት ታደሱ፤ ወጣት ሁኑ -- ይላሉ ፈረንጆቹ።

ኒው ዮርክ ታይምስ ስኴር ላይ የአዲሱን ዓመት መጥባት ወትሮም በየዓመቱ የምታበስረው ኳስ ከ141 ጫማ ወይም ከ43 ሜትር ከፍታ ቁልቁል ስትምዘገዘግ በዚህ ዓመት ጋዜጠኛነትንና ሃሣብን የመግለፅ ነፃነትን ከፍ አድርጎ በማክበር እሳቤ ውስጥ ልዩ ትርጉም ኖሯታል - የዛሬዋ።

ሌላም ኒው ዮርክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ክንዋኔ ነበር፤ በአደባባዩ የተገጠገጠውን (ሚሊዮን ነው የሚሉ አሉ - ቁጥሩ) ታዳሚ ደኅንነት ለመጠበቅ ‘አሉኝ’ የሚላቸውን ዐይኖቹን ሁሉ የከፈተው የከተማዪቱ ፖሊስ ቅኝቱን ለማስፋት ድሮኖችን ተጠቅሟል - ለመጀመሪያ ጊዜ።

ከዋሺንግተን ዲሲና ከኒው ዮርክ ሁለት ሰዓት ቀደም ብላ አዲሱን ዓመት ያስተናገደችው ግዙፏ የደቡብ አሜሪካዪቱ ብራዚል - አትላንቲክ ዳርቻ ላይ ነው የተቀበለችው - ኮፓካባና ቢች። እዚያም ሃገሬውና ከዓለም ዙሪያም የፈረንጅ እንቁጣጣሽ ትንግርት ሊያይ የተኮለኮለ ሌላ ሚሊዮን ነበር አሉ፤ ይበልጣልም የሚሉ አሉ።

በሌላ የዓለም ግንባር፤ በሽብር ጥቃቶች ስትታመስ ባስተዋልናት፤ በፀረ-መንግሥት ዓመፅ ስትናጥ በሰነበተችው ፈረንሣይ ዋና ከተማ ፓሪስ ደግሞ በገናናው ሻምፕዝ-ኤሊዜ ጎዳና ላይ ሺኾች ዳንኪረኞችና የአዲስ ዓመት ፌሽታ የሚንጣቸው ከአር ዶ ትራምፍ /’የድል ቅስት’ እንደማለት ነው/ አናት ላይ የሚፈነጠቁትን፣ የሚዘሩትንና ሰማዩን የሚሞሉትን የብርሃን ኅብረቀለማት ለማየት ተገጥግጠዋል።

እንዲያም ሆኖ ታዲያ ሰልፈኞቹ ቂማቸውን አልሻሩም፤ በዚያ ክብረ በዓል ውስጥም ቢሆን የተቃውሞዎቻቸውን መልዕክቶች ሲያስተላልፉ አምሽተዋል። በርግጥ በሰላም።

ፕሬዚዳንቷ ኢማኑኤል ማክሮንም የትናንትናውን የበዓል ስሜት የፈጠረውን የመረጋጋት ጠባይና የሕዝቡን የአዲስ ዓመት ጥሞና አላባከኑትም። “የሕዝቤን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ የተሻሉ ሥራዎችን ማሳየት እንችላለን” ብለዋል - ሰዉም ሰምቷቸዋል።

ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ላይ በብራንደንበርግ አደባባይ ግዙፍ የሙዚቃ ትርዒት ነበር። ለንደን ላይ እንግሊዛዊያኑ ዓመት ቆጥረው በናፍቆት የሚጠብቁት ቢግ ቤን የማማ ሰዓት በጥገና ምክንያት ድምፁ ተቋርጦ ቢቆይም ለአዲስ ዓመት ሲባል ከተገጠሙለት የውጭ ማገናኛዎች የተለመዱ የተስፋ ዝማሬ ደወሎቹን ቴምስ ወንዝ ዳርና ዳር እንዲሁም በሌሎችም የከተማዪቱ አካባቢዎች ሆነውም የርችቱን እሩምታ ለሚጠብቁ በዓልተኞች አሰምቷል።

እንዲሁም ድንቅ የሆነው የመስኮቡ ቀይ አደባባይ ላይም /“ውብ አደባባይ”ም ሊሆን ይችላል የስሙ ትርጉም/ ታላቅ የሙዚቃ ድግስ ነበር፤ የከተማዪቱ መናፈሻዎችም በርችት ደምቀዋል።

የዱባይን ሰማይ ያለበሱት ርችቶች በዓለም ረዥሙን ሕንፃ ቡርጅ ኻሊፋን ይበልጥ አስውበውት ታይቷል። ሌላም ወሬ አለ፤ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች። ራስ ኻይማ ውስጥ ለ12 ኪሎሜትሮች የተዘረጉት የአዲስ ዓመት ክብረበዓይ ተቀጣጣይና እንቁጥቁጥ መብራቶች በጊነስን የክብረወሰን መዝገብ ሳይሠፍሩ አልቀረም እየተባለም ነው።

ኢንዶኔዥያ ዋና ከተማ ጃካርታ ውስጥ ደግሞ እጅግ ጥብቅ በነበረ የበዓል አከባበር ሁኔታ አራት መቶ ጥንዶች በጋራ በተደገሠላቸው ሠርግ አዱሱን ዓመት በአዲስ ጉልቻ ተቀብለውታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሣቸው ያሉ ጉዳቶች፣ እያደገ የመጣው ያለመቻቻል አዝማሚያ፣ የየአካባቢው ፖለቲካ መከፋፈልና የኑሮ መዛባት የምጣኔ ኃብት አመሳሶና ያለመተካከል እንደሚያሳስበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ትካዜን የሚያጭር መልዕክት አታውቋል። በሌላ በኩል ደግሞ ተስፋ ለመሰነቅም ብዙ ምክንያት አለን ብሏል።

ዓለም በ2019? እንግዲህ አስተውሉ... መልካሙ ሁሉ ይሁን፤ መልካም ያልሆነ ምንም አይሁን።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ

2019
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:39 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG