በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክኒያት በመላው ዓለም የሚገኙ 7.8 ቢሊዮን ሰዎች ያለ የጋራ የደስታና የፍሰሃ ዝግጅት 2020 ዓ.ም በቀዘቀዘ ሁኔታ ተሰናብተውታል። ራሺያ 2021ን የጀመረችው እጅግ ታዋቂ የሆነውን የአዲስ ዓመት ዋዜማ መጀመሪያ ዝግጅቷን በመሰረዝ ነው። ሆኖም ከሞስኮ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ካሉንጋ ውስጥ በጎብኚዎች የሚከበሩ በዓላት እንዲቀጥሉ ተደርገዋል።
ቱርክ አዲስ ዓመትን የተቀበለችው ለአራት ቀናት የሚቆይ እቤት ውስጥ የመቀመጥ ውሳኔን በማሳለፍ ነው። የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረጂብ ታይፕ ኤርዶጋን ይህንን ውሳኔ ተላልፈው በሆቴል ውስጥ ዝግጅት በሚያዘጋጁ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።
በርሊን በወረርሽኙ ምክኒያት በዝምታ ነው ያሳለፈችችው። ፈረንሳይ ያወጣችውን የሰዓት እላፊ ገደብ ለማስፈፀም 100 ሺሕ ተጨማሪ የፀጥታ ሠራተኞችን ጎዳና ላይ አሰማርታለች። ግሪክም እንዲሁ ሰዓት እላፊውን እንደምታስፈፅም አስታውቃለች። እንግሊዝ እና ሕንድም እንዲሁ በእቀባዎች ውስጥ አሳልፈዋል።
በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ በጉጉት የሚጠበቁት የርችት መተኮስ እና የመብራት ትዕይንቶች በዚህ ዓመት እንደታሰቡት አልነበሩም። አዲሱን ዓመትን ቀድማ የምታበስረው አውስትራሊያ ሲዲኒ ከተማ ዘንድሮ ያለ ታዳሚ አሳልፋለች። በቀደሙት ዓመታት ከ1 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚታደምበት የሲዲኒ የባህር ዳርቻ አደባባይ ላይ ለሚታየው የርችት ትርኢት የሚታደሙ ሰዎች ዘንድሮ በየቤታቸው ሆነው በቴሌቭዥን እንዲከታተሉ የአገሪቱ ባለስልጣናት በመወሰናቸው በዓሉ ጭር ባለ ሁኔታ ተከብሯል።
በፍጥነት ከሚሰራጨው አዲሱ አይነት የኮሮናቫይረስ ጋር ትግል የያዘችው ብሪታንያ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ጠበቅ ላይ ትእዛዝ አስተላልፋለች። የርችት መተኮስ እኛ የመብራት ትርኢቶችን ቢያዘጋጁም ሰዎች የተሰበሰቡባቸው ዝግጅቶችን ግን ታጥፈው በቀዝቃዛ ሁኔታ አዲሱን የ2021 ዓ.ም ተቀብለዋል።