በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በማይ ጸብሪ ዐዲስ መፈናቀል መኖሩን ተመድ እና የተራድኦ ድርጅቶች ገለጹ


በማይ ጸብሪ ዐዲስ መፈናቀል መኖሩን ተመድ እና የተራድኦ ድርጅቶች ገለጹ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:28 0:00

ባለፈው ጥቅምት የሰላም ስምምነት ቢፈረምም፣ በአማራ ክልል ያሉ ኃይሎች፣ በ10ሺሕ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ከአጨቃጫቂ ቦታዎች እያፈናቀሉ ነው፤ ሲል የአሶስዬትድ ፐረስ ዜና ወኪል ዘግቧል።

ዜና ወኪሉ መረጃውን፣ ከተመድ እና የረድኤት ድርጅት ሠራተኞች ማግኘቱን፣ እንዲሁም የድርጅቶቹን የውስጥ ሰነዶች መመልከቱን በዘገባው ጠቁሟል።

አወዛጋቢዋ ማይ ጸብሪ፣ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ እና በዐማራ ክልል ወሰን አቅራቢያ የምትገኝና በጦርነቱ ወቅት ተፃራሪ ኃይሎች፣ በመፈራረቅ ሲቆጣጠሯት እንደነበር ያወሳው የአሶሲዬትድ ፕረስ ሪፖርት፣ “የዐማራ ተወላጆች ቦታው የእነርሱ መኾኑን እንደሚናገሩ” አመልክቷል።

ከመጋቢት ወር ወዲህ፣ 47ሺሕ ነዋሪዎች፣ ከማይ ጸብሪ ተፈናቅለው፣ 55 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ወደምትገኘው እንዳባጉና እንደሔዱ የሚያሳይ መረጃ፣ ከተመድ ሰነዶች ላይ መመልከቱን፣ የአሶስዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ገልጿል።

በሌላ የረድኤት ድርጅት የተዘጋጀው ሪፖርት ደግሞ፣ ነዋሪዎቹ ማይ ጸብሪን ለቀው የወጡት፣ በመደበኛ የዐማራ ኃይሎች፣ “በመዋከባቸው፣ እንዲሁም በማንነታቸው ምክንያት በደረሰባቸው ዛቻ” እንደኾነ አመልክቶ፣ ኃይሎቹ ነዋሪዎቹን ”ከመኖሪያቸው አስወጥተዋል” ሲል አክሏል።

ተፈናቃዮቹ እንዳባጉና ከደረሱ ጀምሮ ርዳታ እንዳልተሰጣቸውና በዚኽም ምክንያት ረኀብ ጠንቶባቸው እንደሚገኙ፣ የረድኤት ድርጅቱ በሪፖርቱ ማስፈሩን የኤፒ ዘገባ ጠቁሟል። አኹን በእንዳባጉና የሚገኙት ተፈናቃዮቹ የተጠለሉት፣ ከኤርትራ ለመጡ ስደተኞች በተሠራ ማዕከል ውስጥ መኾኑንና መጠለያው በጦርነቱ ወቅት ክፉኛ መጎዳቱን ሪፖርቱ አመልክቷል። በቅርቡ ወደ መጠለያው ተጉዞ የነበረ የረድኤት ሠራተኛ፣ በሥፍራው ኹኔታው “በጣም መጥፎ” ቢኾንም፣ የተፈናቃዮቹ ቁጥር ግን “በየቀኑ እየጨመረ” እንደኾነ መናገሩን ዘገባው አስረድቷል፡፡

“ጣራው እና ቧንቧው ፈርሷል፤ መጸዳጃ ቤት የለም፤ የክፍሎቹ በሮች እና መስኮቶች ተዘርፈዋል ወይም ፈርሰዋል፤ በቂ የውኃ አቅርቦትም የለም፤” ሲል፣ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የረድኤት ሠራተኛ መናገሩን፣ ዜና ወኪሉ በሪፖርቱ አመልክቷል።

ከዐማራ ባለሥልጣናት ወዲያውኑ አስተያየት ማግኘት አለመቻሉን ዘገባው አስፍሯል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ሌላ ኹለተኛ የረድኤት ሠራተኛ በበኩሉ፣ ከማይ ጸብሪ የተፈናቀሉት አብዛኞቹ ሰዎች፣ ለኹለተኛ ጊዜ የተፈናቀሉ መኾናቸውን ጠቅሶ፣ መጀመሪያም፣ “ምዕራብ ትግራይ” በሚል ከጠራው መኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አውስቷል፤ ሲል ሪፖርቱ አክሏል።

በጦርነቱ መጀመሪያ ወቅት፣ የዐማራ ኃይሎች፣ ምዕራብ ትግራይን ወደ ዐማራ ክልል መቀላቀላቸውን፣ ኃይሎቹም በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ከአካባቢው ካስወጡ በኋላ፣ በአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር “በዘር ማጽዳት” መወንጀላቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል።

በቅርቡ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ ከኹለት ዓመት ክልከላ በኋላ ሰብአዊ ርዳታ ወደ ትግራይ ቢደርስም፣ የዐማራ ኃይሎች በማይ ጸብሪ አካባቢ የምግብ ሥርጭቱን እያገዱ መኾኑንና የነዋሪዎች ግድያም እየተፈጸመ እንዳለ፣ የረድኤት ሠራተኞች ሪፖርት ማድረጋቸውን የኤፒ ዘገባ አመልክቷል።

ባለፈው ኅዳር አካባቢውን ለቆ መውጣቱን፣ ይህም፣ “የትግራይ ዐማፅያንን ትረዳለኽ፤” በሚል የዐማራ ኃይሎች ከአስፈራሩት በኋላ እንደኾነ ተፈሪ ሙለይ የተባለ ነዋሪ መናገሩን ሪፖርቱ አመልክቷል። ተፈሪ አክሎም፣ ባለፈው መጋቢት፣ አቅራቢያው ወደምትገኘው ሃይዳ መንደር ተመልሶ እንደነበር፣ በዚያም የዐማራ ሠራዊት፣ ባህላዊ የወርቅ አንጣሪዎች ላይ ሲተኩስ ማየቱን ተናግሯል፤ ሲል የኤፒ ዘገባ አስፍሯል።

የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ፌዴራል ኃይሎች እና መደበኛ ፖሊስ እንደሚካተቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ካስታወቀ በኋላ፣ በዐማራ ክልል ተቃውሞ መቀስቀሱን፣ እንዲሁም በፌዴራል ሠራዊት እና ትጥቅ መፍታቱን በሚቃወሙ የዐማራ ክልል ኃይሎች መካከል ውጊያ መካሔዱን ሪፖርቱ አውስቷል።

ውሳኔውን ተከትሎ በክልሉ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ግጭት፣ በማይ ጸብሪ ያለውን መፈናቀል እንደሚያባብሰውና በአሁኑ ወቅት፣ 150 የሚደርሱ ቤተሰቦች፣ በየቀኑ እንደሚፈናቀሉ፣ ሌላ የረድኤት ድርጅት መታዘቡን ኤፒ በዘገባው አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG