በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሚኒስትሮች የሹመት ሂደት በምክር ቤቱ ጥያቄ አስነሳ


ከቀኝ ወደ ግራ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያ ሥላሴ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ናቸው።
ከቀኝ ወደ ግራ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያ ሥላሴ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እና የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ናቸው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሔደው የ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለያየ ጊዜ የሾሟቸውን የአምስት ሚንስትሮች ሹመት አፅድቋል።

ሹመታቸው የጸደቀላቸው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያ ሥላሴ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ናቸው።

ከእነዚህ ሹማምንት መካከል ሁለቱ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተሾሙ ሲኾኑ፣ ሦስቱ ደግሞ ባለፈው ጥቅምት ስምንት የተሾሙ ናቸው።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚንስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ የሚንስትሮቹን የትምህርትና የሥራ ልምድ በተመለከተ ማብራሪያ ካቀረቡ በኋላ፣ በምክር ቤቱ አባላት አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል፣ ተሿሚዎቹ ሹመታቸው “በምክር ቤቱ ሳይፀድቅላቸው በሚኒስትርነት እንዲያገለግሉ እንዴት ደብዳቤ ይጻፍላቸዋል” የሚል ይገኝበታል።

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጂጌ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ አሠራሩ የተለመደ እንደሆነ እና ባለፈው ዓመት የተሰጠው የሚኒስትሮች ሹመት ምክር ቤቱ ለክረምት ዕረፍት ሊዘጋ በተዘጋጀበት ወቅት በመሆኑ በምክር ቤቱ ሳይፀድቅላቸው መቆየቱን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ከተከፈተ በኋላ ደግሞ አብዛኛው አባላቱ በሥልጠና እና መሰል ጉዳዮች በቂ ጊዜ ባለማግኘታቸው ሂደቱ መቆየቱን አብራርተዋል።

የሕገመንግስትና ሕገመንግስት ጉዳዮች መምህር እና ተመራማሪ አሮን ደጎል ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት “ሕገመንግሥቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጠው ሥልጣን ለሹመት ያሰባቸውን ሰዎች በዕጩነት ማቅረብ ነው” ይላሉ፡፡

በዕጩነት የቀረቡ ሰዎች ሹመታቸው በምክር ቤቱ ካልፀደቀላቸው “የሚኒስትርነት ሥልጣንን መጠቀም አይችሉም” የሚሉት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ባለሙያው፣ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ነው ብለዋል፡፡

አንድ በሚኒስትር ዕጩነት የሚቀርብ ግለሰብ ሹመቱ ሳይፀድቅለት ምን ያህል ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ የሚደነግግ አለመሆኑ ደግሞ፣ ከጊዜ አኳያ ክፍተትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የሚኒስትሮች ምክር ቤትን የአሰራር ሥርዓት ለመደንገግ የወጡ መመሪያዎች ለዚህ ምላሽ ሊኖራቸው እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

“ሚኒስትሮች ከሥልጣናቸው በሚነሱበት ወቅት ለምን ለምክር ቤቱ ቀርቦ ግምገማ አይካሔድበትም” የሚለው ሌላው በምክር ቤቱ አባላት የተነሳ ጥያቄ ነው፡፡

የሕገመንግስትና ሕገመንግስት ጉዳዮች መምህር እና ተመራማሪ አሮን ደጎልም ይህን ጥያቄ ይጋራሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው፣ ከአካሔድ አንጻር አንድን ሹመኛ ማንሳት የሚችለው የሾመው አካል ምክር ቤቱ ነው መሆን ያለበት የሚል ነው፡፡ ነገር ግን፣ ከፍርድ ቤት ዳኞች የሹም ሽር አካሔድ በተቃረነ መልኩ፣ በምክር ቤቱ የሚሾሙ ሚኒስትሮች ከሥልጣናቸው ሲነሱ በምን መልኩ መሆን እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ አለመደንገጉ በክፍተትነት የሚታይ ነው ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎሽ (ዶ/ር) ሹመት በዛሬው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ከሁለት አባላት ትችት ቀርቦበታል፡፡

ከተቺዎቹ መካከል የሆኑት የአብን ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ “ዶ/ር ጌዲዮን በፍትሕ ሚኒስትርነታቸው ወቅት የዕውቀት ችግር አለባቸው አልልም፡፡ በተለያዩ መድረኮች አይቼአቸዋለሁ፤ ሙያቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው” ካሉ በኋላ፣ “ነገር ግን አፈጻጸማቸውን ካየነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠይቀውን የፍትሕ ጥማት ከማስታገስ እና ከማርካት ይልቅ፣ አሁንም የፍትህ ሥርዓቱ የፖለቲካ መሳሪያ እንዲሆን አድርገዋል” ሲሉ ተችተዋል፡፡

“የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብታችን ሳይነሳ ተጎትተን እንደሽፍታ ስንታሰር እና ለወራት ስንቀመጥ፤ ሌሎች የምክር ቤት አባላትም ተገቢውን ፍርድ ሳያገኙ ለዓመታት ሲንገላቱ ከሳሹ የፍትሕ ሚኒስቴር ምንም የሰራው ነገር የለም” በማለት ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ በመሆኑም የእውቀት ችግር ባይኖርባቸውም የፍትሕ ዘርፉን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱ ስለሆኑ፣ ከላቸውተሞክሮ አንጻር ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ብቁ አይደሉም፡፡ ለዚህ ቦታ መቅረብ የለባቸውም” በማለት ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው “እንደ መሪ ፓርቲም እንደመንግሥትም፣ ዶ/ር ጌዲዮን በፍትሕ ዘርፍ እና ከዚያም በፊት በነበሩበት ኃላፊነት በጣም ውጤታማ አመራር መሆናቸውን በተጨባጭ ገምግመናል” በማለት የአብኑ ተመራጭ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ያነሱትን ሃሳብ ተቃውመዋል፡፡

በምክር ቤት ደረጃ የፍትሕ ዘርፉን የሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴም ዘርፉ ውጤታማ ስለመሆኑ በየጊዜው ሪፖርት አቅርቧል ሲሉም አክለዋል፡፡ “ስለዚህ አጠቃላይ እና ግምታዊ በሆነ መንገድ መፈረጅ የለባቸውም። ፖለቲከኞች እንዲጠየቁ አድርገዋል መባሉ፣ በሕገመንግሥት ከተቀመጠው ድንጋጌ እና ከሌሎችም ሕጎች አኳያ ትንሽ ያፈነገጠ ነው” ሲሉ ዶ/ር ጌዲዮንን ተከላክለዋል፡፡

የምክር ቤቱን ውይይት ተከትሎ ሹመቱ በ1 ተቃውሞና በ2 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ የፀደቀ ሲሆን፣ ከዶ/ር ጌዲዮን ውጭ ያሉት አራቱ አዲስ የተሸሙት ሚኒስትሮች ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቃለ መሃላው ላይ ያልተገኙት፣ አስቀድሞም የመኒስትሮች ምክር ቤት አባል በመሆናቸው ቃለ መሃላውን ስለፈፀሙ እንደሆነ እና ይህ አሰራርም የተለመደ መሆኑን የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG