የኢትዮጵያ መከላከያ "መቀሌ አጠገብ አካሂጃቸዋለሁ" ያላቸው የአየር ድብደባዎች የህወሃትን የጦር መሣሪያ ማምረቻና ማደሻ ለመምታት ያደረገው ዘመቻ አካል እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።
ህወሃት የሚቆጣጠው ትግራይ ቴሌቭዥን ደግሞ የዛሬው ድብደባ የተካሄደው በከተማይቱ ማዕከል እንደሆነ መናገሩን ሮይተርስ አመልክቷል።
በሌላ በኩል ትግራይ ውስጥ ያለውን ኃይል በግማሽ ሊቀንስ እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስታወቁን አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ አንድ ዓመት በሞላው ጦርነት ውስጥ አማፂያኑን የትግራይ ኃይሎች ለማዳከም ባጠናከረው ዘመቻ በክልሉ ዋና ከተማ ላይ ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ የአየር ድብደባ አካሂዷል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዜና ወኪሉ የጠቀሰው በህወሃት የተያዘው የትግራይ ቴሌቪዥን ድብደባው በከተማይቱ መሃል እንደተፈጸመ ቢዘግብም የደረሰን የሰውም ሆነ የንብረት ጉዳትን አስመልክቶ የሰጠው መረጃ እንደሌለ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ
"ህወሃት ጥይትና ከባድ መሳሪያዎችን በእምነት ቦታዎች ላይ መደበቅና መደበኛ የትግራይ ሰዎችን ሰብዓዊ ከለላ ማድረግ ልማዱ ነው" ማለታቸውንም ሮይተርስ ገልጿል፡፡
አነጋግሬያቸዋለሁ ያላቸው ሁለት በመቀሌ የሚገኙ የረድዔት ሠራተኞች ድብደባው መንግሥቱ ለህወሃት ድጋፍ ይሰጣል በሚለው መስፍን ኢንጂነሪንግ ላይ ያነጣጠሩ እንደነበሩ መግለጻቸውን ሮይተርስ ጠቁሟል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ሮይተርስ የት እንደሆነ ካልተገለጸ ቦታ በሳተላይት ስልክ አግኝቻቸዋለሁ ያላቸው የህወሃት መሪ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መንግሥቱ ድብደባውን እያካሄደ ያለው በመሬት ላይ እየተሸነፈ ስለሆነ ለመበቀል ነው ብለው እንደሚያምኑና ድብደባው የመታው ፋብሪካውን ሳይሆን ሌላ የግል ኩባኒያ መሆኑን እንደነገሩት ነገር ግን ዝርዝር እንዳልሰጡት አመላክቷል፡፡
አንድ የመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታል ሃኪምን የጠቀሰው የዜና ወኪል የፍንዳታው ሃይል አንድ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ሆስፒታላቸውን መስኮቶች መሰባበሩን፣ የፋብሪካው ሰራተኛ የሆኑ አራት ሰዎችና በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አንዲት ሴት ቆስለው ለሕክምና እንደመጡ መናገራቸውን ገልጿል፡፡
ምንም እንኳን ድብደባዎች ከትላንት በስቲያ መካሄዳቸውን የመንግሥቱ ቃል አቀባይ በዕለቱ ቢያስተባብሉም የመንግሥቱ መረጃ ማጣሪያ /ፋክት ቼክ/ ዛሬ ባወጣው አጭር መልዕክት
"ጥቃቶቹ ዒላማ ያደረጉት የህወሃትን የጦር መሳሪያ ማምረቻና የጦር ጥገና ጣቢያዎችን ብቻ ነው፤ የመከላከያ ሠራዊት የሚያከናውናቸው እነዚህ ስራዎች የሽብር ድርጊቱ ከባድ የጦር መሳሪያዎችንና ሌሎች ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎችን ለመሸጥ የሚጠቀምባቸውንና ወደ ወታደራዊ መገልገያነት የቀየራቸውን የተወሰኑ ቦታዎች ከጥቅም ውጪ ለማድረግ ያለመ ነው" ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ከበባ ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ አግዷል በሚል ትግራይ ውስጥ ያለውን ኃይል በግማሽ እንደሚቀንስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስታወቁን አሶሺየትድ ፕሬስ ዛሬ ዘግቧል፡፡
ኤፒ የጠቀሳቸው የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ አቅርቦት ቃል አቀባይ ሳቪያኖ አብሬዩ ድርጅቱ የሠራተኞቹን ቁጠር ከ530 ወደ 220 ሳያወርድ እንደማይቀር ተናግረዋል። ድርጅቱ በምግብ እጥረት ምክንያት ሰዎች እየሞቱ መሆናቸውንም አመላክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ ከመቀሌ ወጣ ብሎ በተካሄደው ሁለተኛ የአየር ድብደባ አብድ ሰው መገደሉን እና ዘጠኝ ሰው መቁሰሉን የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ፍርሃን ሃቅ ትላንት ኒውዮርክ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡