በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኔታንያሁ ተቀናቃኝ የአሜሪካ ጉብኝት በእስራኤል ጦር አመራር ውስጥ ክፍተት መኖሩን ያሳያል


ፎቶ ፋይል፡ በኔታንያሁን የጦር ካቢኔ የተቀላቀሉት እና ማዕከላዊ የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሆኑት ቤኒ ጋንቴዝ በቴል አቪቭ፣ እስራኤል፣ እአአ የካቲት 8/2024
ፎቶ ፋይል፡ በኔታንያሁን የጦር ካቢኔ የተቀላቀሉት እና ማዕከላዊ የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሆኑት ቤኒ ጋንቴዝ በቴል አቪቭ፣ እስራኤል፣ እአአ የካቲት 8/2024

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋራ ለመነጋገር እሁድ ዋሽንግተን በገቡት ከፍተኛ የካቢኔ ሚኒስትር ላይ ቁጣቸውን መግለፃቸውን አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን ገለፁ። የኔታንያሁ ቁጣ ከሐማስ ጋር አምስት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ጦርነት እያካሄደ ባለው የሀገሪቱ አመራር መካከል እየሰፋ የመጣውን ክፍተት ያሳያል ተብሏል።

ሐማስ በጥቅምት ወር ያካሄደውን ጥቃት ተከትሎ በኔታንያሁን የጦር ካቢኔ የተቀላቀሉት እና ማዕከላዊ የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሆኑት ቤኒ ጋንቴዝ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጡት፣ በጋዛ የሚታየውን የፍልስጤማውያን ስቃይ በማስቆም እንቅስቃሴ እና ከጦርነቱ በኃላ ሊኖር በሚገው እቅድ፣ በአሜሪካ እና በኔታንያሁ መካከል ያለው አለመግባባት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።

የኔታንያሁ ቀኝ አክራሪ ሊኩድ ፓርቲ አባል የሆኑ አንድ ባለሥልጣን እንደተናገሩት፣ ጋንቴዝ ወደ አሜሪካ የተጓዙት ከእስራኤል መሪ ፈቃድ ሳያገኙ ነው። እኚኽ ማንነታቸው እንዳይገለፅ የጠየቁት ባለሥጣን ጨምረው ኔታንያሁ ከጋንቴዝ ጋር ጠንከር ያለ ንግግር ማድረጋቸውን እና እስራኤል "አንድ ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትር" እንዳላት እንደነገሯቸው አመልክተዋል።

ጋንቴዝ ከዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ኻሪስ እና ከብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ ጄክ ሱሊቫን ጋር ሰኞ እለት ለመነጋገር ቀጠሮ የተያዘላቸው ሲሆን፣ ማክሰኞ እለት ደግሞ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ጋር እንደሚገናኙ የብሄራዊ እንድነት ፓርቲያቸው አባል ገልጿል።

የጋንቴዝ ጉብኝት አሜሪካ ለእስራኤል ጦርነት ያላትን ድጋፍ ለማጠናከር እና እስራኤላዊ ታጋቾችን እንዲፈቱ ግፊት ለማድረግ የታለመ መሆኑን ሌላ ማንነታቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የእስራኤል ባለስልጣን ተናግረዋል።

በመጪው ሳምንት ቅዱስ ረመዳን ፆም ከመጀመሩ በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ በግብፅ የሚካሄደው ድርድር የቀጠለ ሲሆን ለሁለት ጥያቄዎቿ ከሐማስ መልስ እየጠበቀች ያለችው እስራኤል ልዑካን እንዳላከች ማንነታቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ ሦስተኛ የእስራኤል ባለስልጣን ገልጸዋል። እስራኤል የትኞቹ ታጋቾች በህይወት እንዳሉ እና ሐማስ በምትካቸው ምን ያክል የፍልስጤም እስረኞች እንዲለቀቁ እንደሚጠይቅ ለማወቅ እየጠበቀ መሆኑን የእስራኤል ሚዲያዎች ዘግበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG