እንደ አዲስ ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ በስድስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂድ ተወስኖበት የነበረው በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ለሦስት ወራት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ መታገዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ ዛሬ በአወጣው መግለጫ፣ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ መሠረት ህወሓት ለቦርዱ ሐምሌ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ መነሻነት በልዩ ኹኔታ የክልላዊ ፓርቲ የምዝገባና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶት እንደነበር አስታውሷል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነበሩት ስድስት ወራት ውስጥ በቦርዱ ዕውቅና በታዛቢዎች ፊት ጠቅላላ ጉባኤውን በማድረግ አመራሮቹን ማስመረጥ እንዲሁም ሠነዶቹን ከዐዋጁ ጋራ አጣጥሞ ማጽደቅ ይገባው እንደነበርም ጠቅሷል። ፓርቲው ይህን እንዲያደርግም ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት በጻፋቸው ደብዳቤዎች ማሳሰቡን አመልክቷል። “ይሁንና ፓርቲው የዐዋጁንና የመመሪያውን ድንጋጌዎችና የቦርዱን ውሣኔዎች በማክበር የጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሄድ፣ መተዳደሪያ ደንቡን ሳያፀድቅና አመራሮቹን ሳይመርጥ በሕግ የተሰጠው የስድስት ወር ጊዜ ተጠናቅቋል” ይላል መግለጫው። ስለሆነም ፓርቲው በዐዋጅ የተቀመጡ መመሪያዎችን ጥሶ በመገኘቱ ለሦስት ወራት በምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይሣተፍ መታገዱን አስታውቋል።
ፓርቲው እስካሁን በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ ያለው ነገር የለም።
ፓርቲው ሕጋዊ አካሔዶችን ተከትሎ የቦርዱን ውሣኔዎችና ትዕዛዞች በማክበር ጠቅላለ ጉባዔ ለማድረግ የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ለመሥራት ለቦርዱ በጽሑፍ ሲያሳውቅ ግን እግዱ እንደሚነሣ ገልጿል። ፓርቲው በተሰጠው የሦስት ወራት የእግድ ጊዜ ውስጥ የእርምት ርምጃ ሳይወስድ ቢቀር ግን በተቀመጡ አሠራሮች መሠረት የፓርቲው ምዝገባ እንዲሠረዝ ቦርዱ መወሰኑን አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም