በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፖርቶ ሪኮ የ2025ን ዋዜማ ያለ መብራት አሳልፋለች


በደሴቲቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ከተከሰተ በኋላ በሳን ሁዋን ጎዳናዎች በጨለማ ተውጠዋል፤ ፖርቶ ሪኮ
በደሴቲቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ከተከሰተ በኋላ በሳን ሁዋን ጎዳናዎች በጨለማ ተውጠዋል፤ ፖርቶ ሪኮ

በዩናይትድ ስቴትስ ስር በምትተዳደረው ፖርቶ ሪኮ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ ከ1.3 ሚሊየን ሕዝብ በላይ በጨለማ ለማሳለፍ ተገዷል። የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ለመመለስ እስከ ሁለት ቀናት ሊፈጅ እንደሚችልም ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

ሉማ ኢነርጂ የተሰኘው፣ የኤሌክትሪክ ሥርጭቱን የሚቆጣጠረው የግል ኩባንያ፣ በመላው ፖርቶ ሪኮ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ከነበሩ 1.47 ሚሊየን ደንበኞቹ መካከል 90 ከመቶ የሚሆኑት አገልግሎት እንደተቋረጠባቸው አስታውቋል።

ማክሰኞ አመሻሹን ጀምሮ በተቋረጠው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክንያት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ዕቃዎች እና የአየር ማቀዝቀዣዎች ሥራ አቁመዋል። ሆኖም አመሻሹ ላይ ሆስፒታሎች እና የፖርቶ ሪኮ ውሃ እና ፍሳሽ ተቋም የመሳሰሉ ከ700 ሺሕ በላይ ደንበኞች አገልግሎት ማግኘታቸውን ሉማ አስታውቋል።

ድርጅቱ አክሎ፣ የመብራት መቆራረጥ የተከሰተው ከመሬት በታች የሚገኝ የኤሌክትሪክ መስመር በመበላሸቱ ሳይሆን እንደማይቀር አመልክቶ፣ በተቻለ መጠን አገልግሎቱን ለመመለስ እየጣርን ነው ብሏል።

የደሴቷ አስተዳዳሪ ፔድሮ ፒርሉሲ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ በጻፉት መልዕክት ለተፈጠረው ችግር "ማብራሪያ እና መፍትሄ እንዲሰጠን እየጠየቅን ነው" ብለዋል። ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡ ዙሪያ ከፒርሉሲ ጋራ መነጋገራቸው እና የዩናይትድ ስቴትስ የኃይል ሚኒስትር ጄኔፈር ጋርናሆልም የተቋረጠው ኃይል በፍጥነት እንዲመለስ ማንኛውንም ድጋፍ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተመልክቷል።

የኃይል መቋረጡ በደሴቷ ላይ የሚንቀሳቀሱ የንግድ፣ የፓርኮች እና የገበያ ማዕከሎች እንዲዘጉ ያስገደደ ሲሆን፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችም በጣም ውስን አገልግሎት ብቻ እንደሚሰጡ ታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG