በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኔቶ የዩክሬንን መከላከያ የማስተባበር የተወሰነ ሥራ ለመረከብ ተስማማ


በዋሽንግተን ዲሲ ጉባኤ በማድረግ ላይ ያለው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጉባኤ
በዋሽንግተን ዲሲ ጉባኤ በማድረግ ላይ ያለው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጉባኤ

በዋሽንግተን ዲሲ ጉባኤ በማድረግ ላይ ያለው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)፣ ለዩክሬን ‘አስተማማኝ’ ያለውን ወታደራዊ ዕርዳታ የሚያስገኝ ፕሮግራም ሲያጸድቅ፣ ሃገሪቱ ቃል ኪዳኑን ለመቀላቀል የምታደርገውን ዝግጅትም ለመርዳት ወጥኗል።

ፕሮግራሙ በአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስትን ተፈጥሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሥራ ላይ ያለውን ቡድን የሚተካ ሳይሆን ተጨማሪ ድጋፍ የሚሰጥ ነው ተብሏል።

ከአምሳ ሃገራት የተውጣጣው ቡድን ለዩክሬን የሚሰጠውን የጦር መሣሪያ ዕርዳታ ሲያስተባበር የቆየ ሲሆን፣ በአዲሱ ፕሮግራም መሠረት አንዳንዶቹን የቡድኑ ሥራዎች በኔቶ ለመከወን እንደታቀደ ለማውቀቅ ተችሏል።

በአሜሪካ ኮንግረስ ለዩክሬን የሚሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ በተመለከተ በፓርቲዎች እሰጥ አገባ ምክንያት ለወራት መጓተቱና የአውሮፓ ኅብረት ፈንድም መዘግየት ማሳየቱ ጉዳዩ በፖለቲካ ምክንያት እክል ሊገጥመው እንደሚችል ያመላከተ ነው ተብሏል።

የዕርዳታው መዘግየት ሩሲያ በጦር ሜዳው የበላይነት እንድትይዝና የዩክሬን ቶር አዛዦችም የመሣሪያ እጥረት እንደገጠማቸው በአደባባይ ቅሬታ እንዲያሰሙ አድርጓል።

አዲሱ የኔቶ አደረጃጀት፣ ምናልባትም ድርጅቱን በይፋ ሲነቅፉ የቆዩት የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ወደ ሥልጣን ቢመጡ፣ ከእርሳቸው ተጽእኖ ውጩ እንዲሆን የተዘየደ እንደሆነ ባለሥልጣናት በመግለጽ ላይ ናቸው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG