የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዓባል ሃገራት የኔዘርላንዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ሩተ ቀጣዩ የቃል ኪዳኑ ዋና ጸሃፊ አድርገው መርጠዋል።
ድርጅቱ ምርጫውን ያደረገው በዩክሬን ያለው ጦርነት ተፋፍሞ በቀጠለበት እንዲሁም አሜሪካ ቃል ኪዳኑን በተመለከተ ወደፊት የሚኖራት አመለካከት በእርግጠኝነት ባልታወቀበት ሁኔታ ነው። ማርክ ሩተ በመጪው ጥቅምት ሥልጣኑን ይረከባሉ።
የወቅቱ የቃል ኪዳኑ ዋና ጸሃፊ የሆኑትን የቀድሞው የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀንስ ስቶልተንበርግን ለመተካት ሌላው ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት የሮማኒያው ፕሬዝደንት ክላውስ ዮሐንስ ባለፈው ሳምንት ከውድድሩ መውጣታቸውን በማሳወቃቸው፣ የኔዘርላንዱ ማርክ ሩተ ካለ ተቀናቃኝ እንዲመረጡ ሆኗል።
አዲሱ ዋና ጸሃፊ የኔቶ ዓባል ሃገራት ለዩክሬን የሚሰጡትን ድጋፍ ማስቀጠል እንዲሁም ቃል ኪዳኑ በቀጥታ ከሩሲያ ጋራ ወደ ጦርነቱ እንዳይገባ መግታትን የመሰሉ ፈተናዎች ይጠብቋቸዋል ተብሏል።
ለቃል ኪዳን ድርጅቱ ብዙም ሥፍራ የማይሰጡት ዶናልድ ትረምፕ በአሜሪካ ወደ ሥልጣን መመለስ የመቻላቸው ጉዳይም የዋና ፀሃፊው ሌላ ፈተና እንደሚሆን ተነግሯል።
መድረክ / ፎረም