በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኔቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የዩክሬንን ኃይል መልሶ በመገንባት ላይ ያተኩራሉ


የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጀኔራል ጄንስ ስቶልተንበርግ
የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጀኔራል ጄንስ ስቶልተንበርግ

ከዛሬ ጀምሮ በሩማኒያ የሚደረገው የኔቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ሁሉም አጋር አገሮች ለዩክሬን ተጨማሪ እርዳታ የሚያደርጉ መሆኑን መልዕክት የሚያስተላለፉበት ነው ሲሉ የኔቶ ዋና ጸሃፊ ጀኔራል ጄንስ ስቶልተንበርግ ዛሬ ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ ተናገሩ፡፡

የወደመውን የዩክሬን መሠረተ ልማት መልሶ ለመገንባትና የሩሲያን የአየር ጥቃት ለመከላከል ተጨማሪ የመከላከያ መሳሪያዎችን ለመርዳት ይበልጥ መስራት እንዳለባቸው አጋሮቹ መልዕክት ያስተላልፋሉ ብለው እንደሚጠብቁም ዋና ጸሃፊው አስታውቀዋል፡፡

ለሁለት ቀናት ከሚቆየው ስብሰባ በፊት ዋና ጸሃፊው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የሩሲያ ሚሳዬሎች ያወደሟቸውን መልሶ ለመገንባት ዩክሬን ትልቅ ሥራ ይጠብቃታል ብለዋል፡፡

“ጅነሬተሮችንና መለዋወጫ እቃዎችን አበርክተናል፣ አጋሮቹ የወደመውን መሰረተ ልማት መልሶ ለመገንባት እየረዱ ነው” ሲሉም ዋና ጸሃፊው ተናግረዋል፡፡

ህብረቱ ለዩክሬን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋና ጸሃፊው አስታውቀዋል፡፡

“የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለአገራቸው ውድቀት ዩክሬንን በመውረር ምላሽ እየሰጡ ነው” ያሉት ዋና ስቶልተንበርግ የዩክሬንን የውሃ፣ የኃይልና፣ የሙቀት አገልግሎት ሰጭዎችን በማቋረጥ ክረምቱን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀሙበት ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡

ዛሬ ማምሻውን ስብሰባው ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት የዩክሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ይህንኑ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ ብለው እንደሚጠብቁም የኔቶ ዋና ጸሃፊ ተናግረዋል፡፡

በሌላም በኩል ኩሌባ፣ ዩክሬንን ለመጎብኘት ከኢስቶኒያ፣ ፊንላንድ፣ አይስላንድ፣ ላቲቪያ፣ ሊቱኒያ፣ ኖርዌና ስዊድን የመጡትን የኖርዲክን እና ባልቲክ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኪቭ አቀባበል ያደረጉላቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡

“የዚህ ጉብኝት ትልቁና ጠንካራው መልዕክት ዩክሬን ይህን ጦርነት ማሸነፍ አለባት... ስለሆነም የምዕራቡ ዓለም ድጋፍ የበለጠ ጠንካራ መሆን አለበት፣ ያለምንም የፖለቲካ ጣጣ ተጨማሪ ከባድ መሳሪያዎችና እንዲሁም የረጅም ርቀት ሚሳዬሎች ድጋፍ መስጠት ይኖርባቸዋል” ሲሉ የኢስቶኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡርማስ ሬንሳሉ ለሮይተርስ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡

ሬንሳሉ ዩክሬናውያን ብርዱን እንዲቋቋሙ የኤሌክትሪክ ጀነሬቶሮች፣ ሙቀት ሰጭ ልብሶችና የምግብ እርዳታ ለመስጠት ቃል መግባታቸው ተገልጿል፡፡

XS
SM
MD
LG