በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኔቶ ዋና ጸሃፊ የፖላንዱ ፍንዳታ ከዩክሬን አየር መከላከያ ሳይሆን አይቀርም አሉ


የኔቶ ዋና ጸሀፊ ጀኔራል ጄንስ ስቶልተንበርግ
የኔቶ ዋና ጸሀፊ ጀኔራል ጄንስ ስቶልተንበርግ

የኔቶ ዋና ጸሀፊ ጀኔራል ጄንስ ስቶልተንበርግ በምስራቅ ፖላንድ ዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ቢያንስ ሁለት ሰዎችን ገድሏል የተባለው የትናንት ማክሰኞ ፍንዳታ “የሩሲያን ክሩዝ ሚሳዬል ጥቃቶችን ለመመከት በዩክሬን አየር መከላከያ ከተከኮሰ ሚሳዬል” ይመስላል ሲሉ ዛሬ ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ተናገሩ፡፡

ዋና ጸሃፊው ከኔቶ ምክር ቤት አባላት ስብሰባ በኋላ ብራስልስ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኔቶ አጋሮች በተደረገው የቅድመ ግምገማ መስማማታቸውን ገልጸው፣ ምርመራው ግን የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ” ያሉት የኔቶ ዋና ጸሃፊ “ይህ የዩክሬን ጥፋት አይደለም፣ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ህገወጥ ጦርነት እስከቀጠለችበት ድረስ ሙሉ ኃላፊነቱን ትወስዳለች” ብለዋል፡፡

የኔቶ መሪዎችና የቡድን ሰባት አባላት አገራት በኢንዶኔዥያ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የቡድን 20 አባላት ጉባኤ ጎን፣ ዛሬ ረቡዕ ቀደም ብለው በጉዳዩ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከስብሰባው በኋላ ለጋዜጠኞ በሰጡት መግለጫ “በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል የደረሰውን ፍንዳታ አስመልክቶ ፖላንድ የምታደርገውን ምርመራ ለማገዝ ተስማምተናል” ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን አያይዘውም “በትክክል ምን እንደተፈጠረ ማወቃችንን ለማረጋገጥ እሞክራለሁ” ብለዋል፡፡

ፍንዳታውን ተከትሎ በጥድፊያ በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ባይደን የካናዳ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአውሮፓ ምክር ቤት፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣልያን፣የጃፓን፣ የኔዘርላንድ፣ የስፔይን እና የእንግሊዝ መሪዎችን መሰብሰባቸው ተመልክቷል፡፡

“አሁን ባለበት ሁኔታ ሚሳዬሉ የተተኮሰው ከሩሲያው አይመስልም” ያሉት ባይደን “ይህን የሚሞግት የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ቢኖርም ሁኔታውን ሙሉ ለሙሉ እስከንመረምር ድረስ ያንን መግለጽ አልፈልግም ብለዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ጥቃቱን “ዋነኛው የጦርነት አባባሽ” ያሉት ሲሆን፣ በቡድን 20 ስብሰባ ላይ የነበሩት በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ ተወካይ ዲሚትሪ ፖልያንስኪ ፍንዳታው የተፈጠረው በኔቶ እና በሩሲያ መካከል ሆን ተብሎ ጦርነት ለመቀስቀስ ስለተፈለገ ነው ማለታቸው ተዘግቧል፡፡

XS
SM
MD
LG