የብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት፣ ሩስያ በምስራቅ አውሮፓ ሃገሮች ላይ የምትደቅነው አደጋ እያደገ ሄዷል ስለሚባለውና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ፕረዚዳንት ኦባማ ዛሬ ማለዳ ዋርሶ ሲገቡ ብሪታንያና የአውሮፓ ህብረት በሰላም እንደሚለያዩ እተማመናለሁ ብለዋል።
“ከጠቅላይ ሚኒስትር ካምሮን፣ ቻንስለር አንጌላ መርከል ጋርና እንዲሁም አሁን እዚህ በተወያየሁት መሰረት የብሪታንያ የአውሮፓ ህብረት መውጣት በሰላምና በሥነሥርዓት እንዲካሄድ በአመዛዛኝነትና በትብብር አብረው እንደሚሰሩ ሙሉ እምነት አለን።”
ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት መወሰንዋ በአውሮፓ የወደፊት ውህደት ላይ “ከባድ ጥያቄ የሚያስነሳ ቢሆንም” ዩናይትድ ስቴትስ ጽኑ የአውሮፓ ውህደት ደጋፊ መሆንዋ ይቀጣላል ሲሉ ፕሬዚዳንት ኦባማ አስገንዝበዋል።
ፕሬዚዳንት ኦባማ ከሁለት ቀናቱ የኔቶ ጉባኤ በኋላ ወደ ስፓኝ ያመራሉ። ፕሬዝደንት ኦባማ ሀገሪቱን ሲጎበኙ ለመጀመርያ ጊዜ ሊሆን ነው።
ፕሬዚዳንት አባማ ዛሬ ከአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝዳንት ዶናልድ ታስክና ከአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዥን ክላውድ ጃከር ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። የዋይት ሀውስ ቤተ-መንግስት ባለስልጣኖች እንደሚሉት ሶስቱ ባለስልጣኖች የብሪታንያ ከህብረቱ መውጣትን በሚመለከት ስለ ሚደረገው ድርድር ፕሬዝደንት ኦባማ ባቀረቡት ሃሳብ ላይ ተወያይተዋል።
በኔቶ ጉባኤ ላይ አብይ ቦታ የሚይዘው የብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት መውጣት ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ፕሬዝዳንት ኦባማ እስላማዊ መንግስት ነኝ ከሚለው ጽንፈኛ ቡድን የሚሰነዘሩት አሸባሪ ጥቃቶችና ሩስያ በኡክራይን ላይ ፈጸመችው ያሉት ወረራም ለአውሮፓ መጻኢ ዕድል አበይት አደጋዎች ናቸው ማለታቸው ተጠቅሷል።
ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።