የዩናይትድ ስቴትሱ የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ ሰዎችን የጨመረ ወደ ጨረቃ በሚደረግ አዲስ የጉዞ ፕሮግራም የሚሳተፉትን አስራ ስምንት ጠፈርተኞች በይፋ አስተዋወቀ።
አርተሚስ የሚል መጠሪያ በተሰጠውና እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2024 ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች ጨረቃን እንደረግጡ የታለመው ፕሮግራም የሚሳተፉት እንኚህ ዘጠኝ ወንዶችና ዘጠኝ ሴቶች ከመጀመሪያው ቡድን ውስጥ ናቸው።
ከእነኚህም ውስጥ ከፊሉ ከዚህ ቀደም ወደህዋ ተጉዘው የሚያውቁ ሲሆኑ፤ ቪክቶር ግሎቨር እናኬት ሩቢንስ የተባሉትሁለት ጠፈረተኞች ባሁኑ ወቅት “ስፔስ ኤክስ” በተሰኘችው በግል ተቋም የመጠቀች መንኩራኩር አማካኝነት በዓለም አቀፉ የሕዋ አገልግሎት ጣቢያ በማገልገል ላይ ያሉ ናቸው።
ያሁኑም የ”ስፔስ ኤክስ” በረራ በግል መንኩራኩር የተሟላ ቁጥር ያላቸው ጠፈረተኞችን ወደ ሕዋ በማምጠቅ የመጀመሪያዋ አድርጓታል።
የአርተሚስ ቡድን በተጨማሪም ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ የሕዋ አገልግሎት ጣቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያረፉት ሙሉ ሴት ጠፈረተኞች የሁኑበት የጠፈር ጉዞ ሁለት አባላት ክርስቲና ኮች እና ጄሲካ ሚየር የተባሉት ጠፈረተኞችም ይገኙበታል።
በትላንትናው ዕለት ፍሎሪዳ ክፍለ ግዛት ውስጥ በሚገኘው የናሳው የኬነዲ የጠፈር ማዕከል የተካሄደውን ይህን የማስተዋወቂያ ሥነ ሥርዓት የመሩት የዩናይትድ ስቴትሱ ምክትል ፕሬዝዳንት ፔንስ “የነገው የአሜሪካ የጠፈር ተመራማሪዎች” ሲሉ የአርተሚስ ጠፈረተኞችን አወድሰው “መጭው ጊዜ ብሩህ ነው” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።
የመጀመሪያው የአርቴሚስ የተልዕኮ ለሚቀጥለው ዓመት ከተያዘውና እጅግ ግዙፉ መሆኑ ከተነገረለት አዲሱ የናሳ መንኩራኩር ማምጠቂያ ዘዴ በተለይም ወደ ማርስ እና ጨረቃ ለሚደረጉ ጉዞዎች ሰዎችን ለማምጠቅ ከተሰናዳው ኦሪዮን የሚል መጠሪያ የተሰጠው ካፕሱል (የአብራሪዎች እና ቁሳቁሶቻቸው የሚሆኑበት የመንኩራኩሩ አካል) የሚወነጨፍ ሰው አልባ የሙከራ በረራ ነው።
በዚህ የናሳ ዕቅድ መሰረት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2024 የአርተሚስ ጠፈረተኞች ቡድን ጨረቃ ላይ ሲያሳርፍ፤ በአውሮፓውያኑ የቀን ስሌት በ1972ቱ በታሪካዊቱ የአፖሎ ፕሮግራም አማካንነት የተከናወነው የጨረቃ ጉዞ ተልዕኮ ካበቃ በኋላ የመጀመሪያው ሰው ያሳፈረ የጨረቃ ጉዞ መሆኑ ነው።