በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አቶ ታዬ ደንዳአ ሁለት የመንግሥት ባለሥልጣናትን በምስክርነት ፍርድ ቤት አቀረቡ


ፎቶ ፋይል፦ አቶ ታዬ ደንዳአ
ፎቶ ፋይል፦ አቶ ታዬ ደንዳአ

በእስር ላይ ኾነው የቀረበባቸው ክስ በመከታተል ላይ የሚገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰላም ሚኒስትር ደ’ኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ፣ ዛሬ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነበራቸው የመከላከያ ምስክር ማስደመጥ ሂደት፣ ሁለት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመከላከያ ምስክርነት አቀረቡ።

ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው፣ “የሰላም ሚኒስቴር ደ’ኤታ ኾነው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኀይሎች ጋራ በመተሳሰር ለጥፋት ተልእኮ በኅቡእ ተንቀሳቅሰዋል፤” በሚል ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ታዬ ደንዳአ፣ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ቃል ለፍርድ ቤት ማስደመጥ ጀምረዋል።

በዛሬ ችሎት፣ ለምስክርነት የቆጠሯቸው፣ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለምና የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ባልቻ፣ አቶ ታዬ የደኅንነት ስጋት እንደነበረባቸው እንደሚያውቁ መስክረዋል። አቶ ታዬ በሕጋዊ መንገድ የጦር መሳሪያ ስለመያዛቸውን ግን እንደማያውቁ ተናግረዋል።

አቶ ታዬ ደንዳአ ሁለት የመንግሥት ባለሥልጣናትን በምስክርነት ፍርድ ቤት አቀረቡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:13 0:00

ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሕገ-መንግሥትና- ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ችሎት፣ የቀረቡት አቶ ታዬ ደንደአ፣ የቆጠሯቸው ሁለት ምስክሮች ያስረዱልኛል ያሉትን የፍሬ ነገር ጭብጥ ለፍርድ ቤቱ አስቀድመው አስረድተው ነበር።

አቶ ታዬ “ሕገ ወጥ የጦር መሣርያ በመያዝ” ክስ እንደቀረበባቸው አስታውሰው፣ የተጠቀሰው የጦር መሳሪያ ከታጣቂዎች በእርሳቸውና በቤተሰባቸው ላይ ሊሰነዘር ይችላል ካሉት የግድያ ጥቃት ለመከላከል በመንግሥት ፈቃድ መያዛቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሥልጣን ላይ በመጡበት ዓመት በ2010 ዓ.ም. ሰኔ አካባቢ “ኦነግ ወያኔ” ሲሊ የጠሩት ቡድን አቶ ታዬን ለግድያ እንደሚፈልጓቸው መናገራቸውን፣ አቶ ታዬ ለፍርድ ቤቱ በአስረጅነት አቅርበዋል።

አቶ ታዬ አክለው “በ2014 ዓ.ም በከረዩ አባ ገዳዎች ላይ የተፈፀመው ጥቃት በመንግሥት ኃላፊዎች የተቀነባበረ ነው” የሚል አስተያየት በመስጠታቸው ምክር ቤት ውስጥ ሐሳባቸውን እንዳይሰጡ መከልከላቸውን ተናግረዋል። ሦስት ጊዜም “ፖለቲካዊ ግድያ” ሲሉ የጠሩት የግድያ ሙከራ እንደተፈፀመባቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

በክሱ ላይ የቀረበው “ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ” እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከአደጋ ለመከላከል በ2015 ዓ.ም የወሰዱት መሳሪያ መኾኑን አስረድተዋል።

መጀመርያ የምስክርነት ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ የሰጡት፣ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ባልቻ፣ አቶ ታዬ ደንደኣ፣ የደኅንነት ችግር እንዳለባቸው ማወቃቸን ገልጸው፣ ነገር ግን ኃላፊነታቸው ከሚንስትር ዝቅ ያለ በመኾኑ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ሕግ እንደማይፈቅድ አስረድተዋል።

አክለውም፣ በተከሳሹ ቤት ተገኘ ስለተባለው የጦር መሳሪያ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለምም ስለጦር መሳሪያ መታጠቅ ከተከሳሹ ጋራ ያወሩት ነገር እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ሁለቱ ምስክሮች አቶ ታዬ የደኅንነት ስጋት እንደነበረባቸው ብቻ እንደሚያውቁ ገልጸው፣ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ዐቃቤ ሕግ ለምስክሮቹ መስቀለኛ ጥያቄን አቅርቧል። የግራ ቀኝ ክርክሩን ሲያደምጥ የቆየው ፍርድ ቤቱም የማጣሪያ ጥያቄዎችን ተይቋል።

ፍርድ ቤቱም በቀጣይ፣ ቀሪ ሦስት ምስክሮችን ለማድመጥ ለኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት በቀሪ ምስክሮች ዝርዝር ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የአዲስ አበባ ከተማ በኃላፊነት መካተታቸው ፍርድ ቤቱ ጠቁመ ነበር።

አቶ ታዬ ከዚህ ቀደም በነበራቸው ችሎት ፣ ጠበቃ እንዳይወክላቸው የሀገሪቱ ደህንነት መሥራያ ቤት ጠበቆችን አስፈራርቶብኛል በሚል አቤቱታ ማቅረባቸው ይታወሳል። ዛሬም ችሎት ፊት ቀርበው የተከራከሩት ከጠበቃ ውጪ ነው።

/ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ያድምጡ/

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG