በሞዛምቢክ ያለው ድህረ ምርጫ አለመረጋጋት ተበብሶ በቀጠለበት ወቅት፣ ከ1ሺሕ 500 በላይ እስረኞች በከፍተኛ ጥበቃ ሥር የነበረን እስር ቤት ሰብረው ወጥተዋል።
እስረኞቹ አመለጡ የተባለው ከመዲናዋ ማፑቶ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘውና ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግበት ከነበረ እስር ቤት ነው።
ለማምለጥ ባደረጉት ጥረትም ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች ጋራ በተነሳው ግጭት 33 ሲገደሉ 15 የሚሆኑት ቆስለዋል።
በሃገሪቱ ሠራዊት አጋዥነት በተደረገው ፍለጋ 150 የሚሆኑት ተይዘዋል ተብሏል። ሰላሳ የሚሆኑት እስረኞች በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ጥቃት ከሚፈጽሙ ቡድኖች ጋራ ግንኙነት እንዳላቸው ተጠቁሟል። ይህ አሳሳቢ እንደሆነባቸው የሃገሪቱ ፖሊስ አዛዥ አስታውቀዋል።
ከእአአ 1975 ጀምሮ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው የፍሬሊሞ ፓርቲ ባለፈው መስከረም መጀመሪያ ላይ በተደረገው ምርጫ አሸናፊ መሆኑ ከታወጀ ወዲህ በሃገሪቱ በርካታ ሕይወት የቀጠፈ ተቃውሞ ለሳምንታት ተካሂዷል።
የገዢው ፓርቲ እጩ ዳንኤል ቻፖ አሸናፊ እንደሆኑ ቢነገርም፣ በአብዛኛው ወጣቶች የሆኑ የተቃዋሚው ቬናሲዮ ሞንድላኔ ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ በተደረገ ተቃውሞ ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ ቢያንስ 21 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
እስከ አሁን 150 ሰዎች ከምርጫው ጋራ በተያያዘ ሁከት ህይወታቸው አልፏል።
መድረክ / ፎረም