በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሰማንያ ሁለት ኢትዮጵያውያን ሞዛምቢክ ውስጥ መያዛቸው ተነገረ


የሞዛምቢክ ካርታ
የሞዛምቢክ ካርታ

ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያመሩ የነበሩ ናቸው የተባሉ ሰማንያ ሁለት ኢትዮጵያውያን በሞዛምቢክ ፖሊስ እንደተያዙ ምንጮች ለቪኦኤ ተናግረዋል።

የሕገ ወጥ ዝውውር ቡድን አባል ነው የተባለና ኢትዮጵያውያኑን ሲመራ የነበረ ግለሰብም መያዙ ተነግሯል።

ሰማንያ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን በፈረስ በሚጎተት እና አትክልት እና ፍራፍሬ በሚያመላልስ፣ የደቡብ አፍሪካ ታርጋ በለጠፈ ተሳቢ ውስጥ ሆነው ሲጓዙ እንደነበር ምንጮች ገልፀዋል። ኢትዮጵያኑ እና ሕገ ወጥ አዘዋዋሪ ነው የተባለው ግለሰብ የተያዙት፣ የሕገ ወጥ ፍልሰተኞች እንደሚበዙባት በሚነገረውና ማኒካ በተባለች የሞዛምቢክ አውራጃ እንደሆነም ታውቋል።

ኢትዮጵያውያኑን ሲመራ የነበረው የሕገ ወጥ ዝውውር ቡድኑ አባል በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተያዘ ሁለተኛው አባል እንደሆነም ታውቋል።

በተደረገው ማጣራት ኢትዮጵያውያኑ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንደገቡ የአካባቢው የፍልሰተኞች አገልግሎት ቃል አቀባይ የሆኑት አቢሊዮ ማቴ ተናግረዋል።

ወደ አገራቸው የመመለስ ሂደት መጀመሩን የጠቆሙት አቢሊዮ ማቴ፣ በቅድሚያ ግን እንዴት ወደ ሞዛምቢክ እንደገቡ የሚጣራ ሲሆን፣ ለጊዜው የተሰወረውን ሾፌርም ለማግኘት በፍለጋ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ካለ ምግብ እና ውሃ ማላዊ ውስጥ ለረዥም ግዜ ቆይተው ወደ ሞዛምቢክ እንደዘለቁ ከተያዙት ኢትዮጵያውያን አንዱ መናገሩም ተጠቁሟል።

ባለፈው ግንቦት 15 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በሞዛምቢክ በአንድ የመቃብር ስፍራ ተሰባስበው ሳለ የተገኙ ሲሆን፣ ከሥስት ዓመታት በፊት ደግሞ፣ 64 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በአንድ የዕቃ ማጓጓዣ ኮንቴይነር ውስጥ ሆነው ሲጓዙ ታፍነው መሞታቸው ይታወሳል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG