ከሰባት መቶ በላይ ፍልሰተኞችን ሜዲተራኒያን ባህር ላይ እርዳታ ሰጪ መርከቦች ደርሰው አተረፏቸው።
ባለፉት ቅዳሜ እና ዕሁድ ጀልባዎች ላይ የተሳፈሩ ከሰባት መቶ የሚበልጡ ፍልሰተኞች ሜዲተራኒያን ባህር ሊቢያ እና ማልታ ጠረፍ አካባቢ እርዳታ ለመስጠት ባህሩን የሚቃኙ መርከቦች ደርሰው ህይወታቸውን እንዳተረፉ ተዘግቧል።
“ኤስኦኤስ ሜዲተራኒ” የተባለው ሜዲተራኒያን ባህር ላይ ሰብዓዊ እርዳታ ለመስጠት የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ቡድን ያሰማራው መርከብ ካለፈው ቅዳሜ ወዲህ በባህሩ ዓለም አቀፍ ክልል ስድስት ስምሪቶች ማሄዱን አስታውቋል።
ቅዳሜ ሌሊት መርከቡ ሲ ዋች ከተባለ የጀርመን በጎ አድራጊ ቡድን መርከብ ጋር በትብብር ተንቀሳቅሶ ባህሩ መሃል ውሃ እየገባበት ከነበረ ደካማ ጀልባ ላይ አራት መቶ ፍልሰተኞችን ማውጣታቸው ተገልጿል።
የፈረንሳዩ ኦሺን ቫይኪንግ መርከብ ቀደም ብሎ አንድ መቶ ስድስት ፍልሰተኞችን አደጋ ላይ ከነበረ ጀልባ አውጥቶ አሳፍሮ የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ ሴቶች እና ህጻናትን ጨመሮ አምስት መቶ ሃምሳ አምስት ሰዎች አሳፍሮ የትኛው ወደብ ላይ ማድረስ እንዳለበት እያሰበበት መሆኑን ገልጿል።
የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮምሽነር የፈረንሳይ ቢሮ ተጠሪ በሰጡት ማሳሰቢያ የፍልሰተኞቹን ጉዳይ ለሜዲተራኒያን ባህር አዋሳኝ ሃገሮች መተው ሳይሆን አዲስ የሚገቡትን ሰዎች ሀገሮች ተከፋፍለው የሚቀበሉበት መንገድ መታቀድ እንደሚኖርበት በቅርቡ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት በማዕከላዊው የባህሩ ክልል በኩል የደረሱት 50,000 አይሞሉም፤ ስለዚህ ተከፋፍሎ መቀበሉ የሚያቅት ነገር አይደለም ብለዋል።
የዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት አይኦኤም ቃል አቀባይም ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል።