ከአንድ ወር በፊት፣ ከኬፕ ቨርዴ ተነሥተው ወደ አውሮፓ እያቀኑ ከነበሩ፣ ከ100 በላይ ሴኔጋላውያን ፍልሰተኞች ውስጥ፣ ከ60 በላይ የሚሆኑት፣ በባሕር ሰጥመው ሳይሞቱ እንዳልቀረ፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) አስታውቋል።
ፍልሰተኞቹ በተሳፈሩበት ጀልባ ላይ፣ ሰባት አስከሬኖች እንደተገኙና የደረሱበት ያልታወቁ 56 ተሳፋሪዎች ደግሞ ሳይሞቱ እንዳልቀረ፣ ድርጅቱ አክሎ አስታውቋል።
የሴኔጋል የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ 38 ፍልሰተኞችን ከኬፕ ቨርዴ የባሕር ዳርቻ እንደታደገ አስታውቋል።
ፍልሰተኞቹን ያገኛቸው፣ የስፔን ዓሣ አስጋሪ መርከብ ነው፡፡ አንድ የስፔን የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጀት እንዳለው፣ ፍልሰተኞቹ፥ በአንድ ትልቅ የዓሣ ማስገሪያ ጀልባ ላይ ሆነው፣ ከአንድ ወር በፊት ከሴኔጋል እንደተነሡ አውስቷል።
ኬፕ ቨርዴ፣ ፍልሰተኞች ወደ ስፔን በሚያደርጉት አደገኛ የባሕር ጉዞ መሥመር ላይ ትገኛለች፡፡ በየዓመቱ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን ያጣሉ፤ ሲል አሶሽየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
መድረክ / ፎረም