ዋሺንግተን ዲሲ —
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአንዳንዶቹ ስፍራዎች ያሉት የኮሮናቫይረስ ተጋላጮች ተጨባጩ ቁጥር በይፋ ሪፖርት ከሚደረጉት አሃዞች ከሁለት እስከ አሥራ ሦስት ከመቶ እጥፍ ይበልጣል ተባለ።
የሃገሪቱ ብሄራዊ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከላት/ሲዲሲ/ ባወጣው ጥናት ከዚህ ድምዳሜ የደረሰው ኒውዮርክ ከተማ፣ ደቡባዊ ፍሎሪዳ፣ ሚዙሪ፣ ዩታህና ዋሽንግተን ክፍለ ግዛቶችን ጨመሮ በአሥር የሃገሪቱ አካባቢዎች ለመደበኛ ምርመራ የተሰጡ የደም ናሙናዎችን ተመርኩዞ መሆኑን አስታውቋል።
ሚዙሪ ውስጥ በተጨባጭ ለቫይረሱ የተጋለጡት ሰዎች ቁጥር በይፋ ከተሰጡት አሃዞች በአሥራ ሦስት እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል፤ ዩታህ ውስጥ ደግሞ በሁለት እጥፍ እንደሚበልጥ ተገልጿል።
የህክምና ባለሙያዎች ማኅበር የምርመር መጽሄት ላይ የታተመው የዚህ ድምዳሜ አቅራቢዎች ቫይረሱ ኖሮባቸው ህክምና ፍለጋ ያልሄዱ ወይም ደግሞ የህመም ስሜታቸው ያልከፋ ሆኖ ወይም ጨርሶ ህመም ስላልተሰማቸው ቫይረሱ ይኖርባቸው እንደሆን ያልተመረመሩ እንዳሉ ያስረዳሉ። በመሆኑም ቫይረሱን ማኅበረሰብ ውስጥ ያዛምቱታል።