በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ሁኔታ የዳሰሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ


የኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ሁኔታ የዳሰሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:03 0:00

የኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ሁኔታ የዳሰሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ በኢትዮጵያ እንደሚያደርጉት የሚጠበቀው ጉብኝት፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን የሐሳብ ልዩነት ለማጥበብ የሚደረግ ዲፕሎማሲ አካል መኾኑን፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም፣ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ ስለ ጉብኝቱ አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ፣ ለአንድ ሳምንት ጉብኝት ያደርጋሉ የተባሉት ልዩ መልዕክተኛው፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋራ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡

በሌላ ዜና፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል የተጀመረው የሰላም ውይይት እንደተቋረጠ መኾኑን፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ቃል አቀባይም እንዲሁ፣ “ከመንግሥት ጋራ የቀጠለም ኾነ የታቀደ ውይይት የለም፤” ብሏል፡፡ በሌላ በኩል፣ በሁለቱ አካላት መካከል ግጭቶች መቀጠላቸው ይታወቃል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ የሚገኙት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢም፣ ትላንት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት ጽሑፍ፣ “እየተናፈሰ ካለው ወሬ በተፃራሪ፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እና በመንግሥት መካከል፣ የቀጠለም ኾነ የታቀደ ውይይት የለም፤” ብለዋል።

አቶ ኦዳ አክለውም፣ አሁን ላይ፣ ሁለተኛ ዙር ንግግር ባይዘጋጅም፣ ለሰላማዊ መፍትሔ ቁርጠኞች እንደኾኑና ወደፊት የሚደረግ ድርድር ወዲያውኑ ይፋ እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

ችግሩ በውይይት እንዲፈታ፣ ከኅብረተሰቡ እና ከልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ አካላት፣ ተደጋጋሚ ጥሪዎች እየቀረቡ ቢኾንም፣ ከመጀመሪያው ዙር ውይይት ወዲህ በቀጠሉት ግጭቶች ሳቢያ፣ ስለ ውይይቱ ቀጣይነት የሚጠቁሙ አዝማሚያዎች አልታዩም፡፡

በሌላ በኩል፣ በምዕራብ ኦሮሚያ በቀጠለው ግጭት ምክንያት፣ በአካባቢው ሰብአዊ ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉን፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA)፣ ሰሞኑን ባወጣው የኹኔታ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ በሪፖርቱ እንደተገለጸው፣ በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ 859 ሺሕ ያህል

ዜጎች፣ በደኅንነት ስጋት ውስጥ ከመኾናቸውም በተጨማሪ፣ የማኅበራዊ እና ሰብአዊ አገልግሎቶችን አያገኙም፡፡

አምባሳደር መለስ፣ በዛሬው መግለጫቸው ያነሡት ሌላው ጉዳይ፣ በሱዳን ያለውን ግጭት በመሸሽ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎችን የተመለከተ ሲኾን፣ እስከ አሁን ገብተዋል ካሏቸው ከ30 ሺሕ በላይ ሰዎች ውስጥ የሚበዙት ኢትዮጵያውያን እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደኾነ የገለጸው ኦቻ በበኩሉ፣ በመተማ ድንበር ብቻ እንኳን፣ ከ33ሺሕ400 በላይ ሰዎች መግባታቸውን አመልክቷል፡፡

በሌላ ዜና፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ ከግንቦት 15 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በቻይና ስኬታማ ጉብኝት ማድረጋቸውን የገለጹት አምባሳደር መለስ፣ ለቻይናውያን የዐማርኛ ትምህርትን በመስጠት ላይ በሚገኘው፣ በቤጂንግ የዓለም አቀፍ ጥናት ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጁ፣ ሦስት የዐማርኛ መማሪያ መጻሕፍት ምረቃ ላይ መታደማቸውንም ተናግረዋል፡፡

በዐማርኛ ቋንቋ ትምህርት፣ ለምረቃ የደረሱ ተማሪዎች መኖራቸውንም የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ይህም፣ የሁለቱን ሀገራት፣ የባህል እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንደሚያጠናክር አስገንዝበዋል፡፡

XS
SM
MD
LG