አምስት ሰዎችን ይዛ ባለፈው እሁድ ወደ ባህር የጠለቀችውና ደብዛዋ የጠፋው ሰርጓጅ ጀልባ፣ የያዘችው ኦክሲጂን ዛሬ ሐሙስ እንደሚያልቅ ሲጠበቅ፣ ፍለጋው ተጧጡፎ ቀጥሏል።
ለ96 ሰዓት ሊያቆይ የሚችል መጠን ያለው ኦክሲጅን ይዛ፣ አምስት ቱሪስቶችን አሳፍራ፣ ከሴይንት ጆን፣ ካናዳ ባህር ዳርቻ ባለፈው ዓርብ የተነሳችው ሰርጓጅ ጀልባ፣ ከመቶ ዓመት በፊት የታይታኒክ መርከብ ወደሰጠመችበት አካባቢ በመጓዝ፣ ከዛም ወደታች 4 ኪ.ሜ ከባሕሩ ጠልቃ በመቅዘፍ ላይ ነበረች። ከእሁድ አንስቶ ግን ከተቆጣጣሪዋ እናት መርከብ ጋር የነበራትን ግኑኝነት አቋርጣለች፡፡
ለተጓዦቹ ሕይወት የሚሰጠው የየያዘችው ኦክሲጅን ዛሬ ሐሙስ ማለዳ እንደሚያልቅ ሲገመት፣ ዓለም አቀፍ የባህር ጉዳይ አዋቂዎች እና የነፍስ አድን ሠራተኞች በውስጧ ያሉትን ሰዎች በሕይወት ለማግኘት ርብርባቸውን ቀጥለዋል።
በውስጧም አንድ የታይታኒክ ታሪክ አዋቂ፣ ፓኪስታናዊ አባት እና ልጅ፣ አንድ አውሮፕላን አብራሪ እና አንድ እንግሊዛዊ ተጓዥ ይገኙበታል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት 46 የሚሆኑ ተጓዦች ታይታኒክ ወደ ሰመጠችበት አካባቢ በሰማጭ ጀልባዋ ጠልቀው የመጎብኘት ዕድል እንደነበራቸው ለማወቅ ይተችሏል።