በትላንትናው ዕለት የተጀመረው ሰልፍ በዛሬ ዕለት መቀጠሉንና ሰልፉም ወደ ግጭት ማምራቱን ጠቁመዋል። በተፈጠረው ግጭት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ወጣቶች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል ተብሏል። በተጨማሪምም ከአረርቲ ከተማ ወጥጣ ብሎ የሚገኝ የችፑድ ፋብሪካ መቃጠሉ ታውቋል።
ስማቸውና ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በሰልፉ ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ የተናገሩ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የመብራት መጥፋቱ ችግር ተደጋጋሚ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ መፈክር አሰምተዋል።
በተጨማሪም የዘይትና ስኳር አቅርቦት ይስተካከል፣ ትክክለኛ የግብር አከፋፈል ሥነ ሥርዓት ይኑር፣ የሚሉና በወጣቶች የሥራ ዕድልና በከተማዋ ፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ ጥያቄዎች ሲነሱ ነበር ተብሏል።
ይህንኑ ሰልፍና ግጭት በተመለከተ ከአማራ ክልል መንግስት ቃል አቀባይ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መረጃን ለማግኘት በእጅ ስልካቸው ላይ ደውለን የነበረ ቢሆንም ስልካቸውን ባለመነሳቱ ምላሻቸውን ማግኘት አልቻልንም።
በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ግን ሰልፉና ግጭት መኖሩን አረጋግጠው “በምንጃር ወረዳ አረርቲ አካባቢ በነበረው ሁከት በአካባቢው በመገንባት ላይ የሚገኘውን ኢንዱስትሪ ፓርክም ጀነሬተሮች ለማቃጠል ሙከራ የተደረገ ሲሆን ይህ ህብረተሰቡ በመከላከሉ ምንም ጉዳት አልደረሰም። የችፑድ ፋብሪካው ግን ከመኪናዎቹ ጭምር ጉዳት ደርሶበታል። ሁለቱ ጉዳት የደረሰባቸው ወጣቶች በአረርቲ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛሉ።” ብለዋል።
(የዚህን ዘገባ ዝርዝር በነገው ምሽት ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን።)
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ