ኢትዮጵያ፣ ከዘጠኝ ዓመት በፊት፣ በዓለም ገበያ ቦንድ በመሸጥ ላገኘችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር፣ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ መክፈል የነበረባትን ወለድ ያልከፈለችው፣ ኹሉንም አበዳሪዎቿን በእኩል ለማስተናገድ እንደኾነ፣ የንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ታኅሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ደ’ኤታ ዶር. ኢዮብ ተካልኝ፣ ከውጭ አበዳሪዎች ጋራ እንደተወያዩ ጠቅሷል፡፡ በውይይቱም፣ የዩሮ ቦንድ ወለድን ላለመክፈል የተወሰነው በዐቅም ማነስ ሳይኾን፣ ከሌሎች አበዳሪዎች ጋራ እየተካሔዱ ያሉት ውይይቶች እንዳይደናቀፉ በማሰብ እንደኾነ ማስረዳታቸውን ገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ፣ የፋይናንስ አስተዳደር ባለሞያ ዶር. አብዱልመናን መሐመድ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በዕዳ ክፍያ ሽግሽግ ጉዳይ፣ ከግል ተቋማት አበዳሪዎቹ ጋራ እየተደራደረ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በዚኽም ስምምነት ላይ እንደሚደረስ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ይህ ካልኾነ ግን፣ አገሪቱ፥ “ዲፎልት” እየተባለ ወደሚገለጸው ዕዳን ለመክፈል ያለመቻል ኹኔታ ውስጥ ስለምትገባ፣ ኢኮኖሚያዊ ጫናው ከባድ እንደሚኾን፣ ባለሞያው አመልክተዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም