በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ክልል የረድኤት አቅርቦት መጓተቱ ሚሊዮኖችን እንዳያሳጣ አስግቷል


በትግራይ ክልል የረድኤት አቅርቦት መጓተቱ ሚሊዮኖችን እንዳያሳጣ አስግቷል
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:16 0:00

በትግራይ ክልል የረድኤት አቅርቦት መጓተቱ ሚሊዮኖችን እንዳያሳጣ አስግቷል

በትግራይ ክልል አስቸኳይ ርዳታ ከሚያስፈልጋቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ውስጥ፣ ርዳታ እያገኙ ያሉት ጥቂቶቹ ብቻ እንደሆኑ፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ ተመለከትሁት ያለውን የሰብአዊ ተቋማት የውስጥ ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሚመራ የትግራይ ክልል የምግብ ርዳታ ማስተባበሪያ ቡድን በጻፈው መልዕክት፣ የረድኤት ተቋማት በዚህ ወር በክልሉ እንዲረዱ በዕቅድ ከያዟቸው 3ነጥብ2 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ፣ እስከ አሁን ድጋፉ የደረሳቸው 14 ከመቶዎቹ ብቻ እንደሆኑ አስታውቋል።

ሰብአዊ ተቋማት ሥራቸውን እንዲያፋጥኑ አክሎ ያሳሰበው ቡድኑ፣ “በክልሉ ፈጣን ርምጃ አለመውሰድ፣ በክረምቱ ወቅት ለከፍተኛ የምግብ ዕጦት እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚዳርግና ተጋላጭ ሕፃናትንና ሴቶችን ሕይወት ሊያሳጣ እንደሚችል” አስጠንቅቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ዩናይትድ ስቴትስ፣ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር፣ ለርዳታ የሚቀርበው እህል እየተዘረፈ እንደሆነ ደርሰንበታል፤ በሚል ርዳታ አቋርጠው የነበረ ሲሆን፣ ከሰኔ ወር ወዲህ ግን ርዳታው መቀጠሉ ይታወሳል። ሆኖም፣ የርዳታ አቅርቦቱን ለመከታተል በተደረጉት ለውጦች ላይ ባጋጠሙ ችግሮች እና በገንዘብ እጥረት ምክንያት፣ በአቅርቦቱ ላይ ትልቅ መጓተት እንደተፈጠረ፣ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሁለት የረጂ ተቋማት ሠራተኞች ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል።

ሌላ ሦስተኛ የርዳታ ሠራተኛም፣ ተቋርጦ የቀጠለው ርዳታ አቅርቦት መጓተቱ፣ በትግራይ የሚገኙ አንዳንድ ተረጂዎች ከአንድ ዓመት በላይ ምግብ እንዳያገኙ ማዘግየቱን ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ጠቁሟል።

በመላው ኢትዮጵያ፥ በድርቅ፣ በግጭት እና በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ ተቋርጦ የነበረው ርዳታ የረኀብ አደጋው እንዲጨምር አስተዋፅኦ አድርጓል።

በአፋር፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎችም፣ የሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ከ15ነጥብ9 እስከ 47 በመቶ እንደሚደርስ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚመራ የኢትዮጵያ ሥነ ምግብ ክላስተር ቡድን ሪፖርት ማመልከቱን አሶሺዬትድ ፕሬስ ጠቅሷል።

ይህም ኾኖ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት፣ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የረኀብ ችግር አለ፤ የሚለውን ሪፖርት አይቀበለውም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG