የአውሮፓ ኅብረት ሕግ አውጪዎች፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ፣ እ.አ.አ ሚያዝያ 10 ቀን የተሻሻለውን የፍልሰት ሥርዓት አጽድቀዋል፡፡
የቀኝ አክራሪው ክንፍ እያገኘ ያለውን ድጋፍ ለመግታት የሚሻው የኅብረቱ የፖለቲካ ማዕከል፣ በሰኔ ወር ከሚካሔደው ምርጫ አስቀድሞ፣ በዘፈቀደ የሚመጡ ፍልሰተኞችን ለመቀነስ ቃል ገብቷል፡፡
የማሻሻያው ዋና ዓላማም፣ ከአውሮፓ ኅብረት ክልል ውጭ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከአፍሪካ የሚመጡ ያልተፈለጉ ፍልሰተኞችን የቆይታ ጊዜ እና የጥገኝነት ጥያቄ መቀነስ ነው፡፡ በማሻሻያው፣ ወደ የአገራቸው የሚመለሱ ፍልሰተኞችን ቁጥር ለመጨመርም ታቅዷል፡፡
በኅብረቱ 27 አባል ሀገራት መካከል ለስምንት ዓመታት ከዘለቀው ውዝግብ በኋላ፣ በአስማሚነት የቀረበው ሐሳብ፣ እንደ ጣሊያንና ጀርመን ባሉ የበለጸጉ መዳረሻ ሀገራት መካከል ያለውን የግዴታ ሚዛን አስቀምጧል፡፡
ይኹን እንጂ፣ ስደትን ለማስቆም ብዙ ርቀት መሔድ ባለመቻሉ፥ በፀረ ኢሚግሬሽን፣ በኅብረቱ ተቃዋሚ አውሮፓውያንና ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ተተችቷል፡፡
ግራ ዘመም ተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾች ግን፣ “በሰብአዊ መብቶች ላይ ትልቅ ጉዳት ያደርሳል፤” ሲሉ ኮንነውታል።
ድምፁ የተሰጠው፥ የአውሮፓ ኅብረት የፖለቲካ ማዕከል፣ ከሁለት ወራት በኋላ በሚካሔደው የአውሮፓ ኅብረት የፓርላማ ምርጫ፣ መቀመጫዎችን ያገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው የቀኝ አክራሪ፣ መጠነ ሰፊ የተቃውሞ ግፊት ከገጠመው በኋላ ነው፡፡
የሕግ አውጭ አካላት፣ “አይኾንም ብላችሁ ድምፅ ስጡ” በሚል፣ በሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተቃውሟቸውን ያሰሙ የነበሩ ተቃዋሚዎች በፈጠሩት ሁከት፣ ድምፅ የመስጠቱ ሒደት ለአንድ አፍታ ተስተጓጉሏል፡፡
ሕግ አውጭዎች በስምምነቱ ላይ ተከራክረው ድምፅ በሚሰጡበት ወቅት፣ ከምክር ቤቱ ውጭ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች የጠሩት አነስተኛ ሰልፍም ተካሒዷል፡፡
ሲቢሪጅ የተባለው ለትርፍ ያልተቋቋመው ድርጅት ቃል አቀባይ ጆሀንስ ሩከርል፣ “ማዕከላዊው ፓርቲ፣ የቀኝ አክራሪዎችን ፍላጎት እያራመደ ነው፤” በሚል ውሳኔውን ተቃውመውታል፡፡
ቃል አቀባዩ አያይዘውም፣ “ይህ የስደተኞች ሕግ ምንም የሚያሻሽለው ነገር ባለመኖሩ እንቃወማለን፡፡ ነገሮችን የበለጠ የከፉ ያደርጋል፤” ያሉት ቃል አቀባዩ፣ በዚህ ውሳኔ “ሰብአዊ መብቶች ይገደባሉ፡፡ ሰዎች ይበልጥ ለአደጋ እንዲጋለጡ ያደርጋል፡፤” ብለዋል፡፡
ፖላንድ፣ ከድምፅ አሰጣጡ በኋላ፣ ስደተኞችን የኅብረቱ አባላት በሆኑ ሀገራት ውስጥ ከፋፍሎ የማስፈርን የአውሮፓ ኅብረትን ዕቅድ እንደማትቀበል አስታውቃለች፡፡ ይህ ተቃውሞ ብቻውን ግን፣ አብዛኛው አባል ሀገራት፣ በዚህ ወር መጨረሻ በማኅተማቸው ያጸኑታል ተብሎ የሚጠበቀውን ማሻሻያው ለማቆም አይችልም።
የአውሮፓ ኅብረት አባላት ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ሁለት ዓመት ቢኖራቸውም፣ ተንታኞች ግን በአንድ ሌሊት ምድር ላይ ያለውን እውነታ ይለውጠዋል፤ ብሎ ማሰብ እንደማይቻል አስጠንቅቀዋል፡፡
በሮይተርስ የተጠናቀረውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም