በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሞሪታንያ ዳርቻ ጀልባ ተገልብጦ የ89 ፍልሰተኞች ህይወት አለፈ


ፎቶ ፋይል፦ የኑዋዲቡ ወደብ፣ ሞሪታኒያ፣ ቅዳሜ፣ እአአ ህዳር 27/2021
ፎቶ ፋይል፦ የኑዋዲቡ ወደብ፣ ሞሪታኒያ፣ ቅዳሜ፣ እአአ ህዳር 27/2021

ወደ አውሮፓ ይጓዙ የነበሩ ፍልሰተኞች የተሳፈሩበት ጀልባ ሞሪታኒያ የባህር ዳርቻ ላይ ተገልብጦ ወደ 90 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን የሀገሪቱ መንግስት መገናኛ ብዙሃን እና አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ትላንት ሐሙስ አስታወቁ። ሌሎች በርካታ ፍልሰተኞች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

የሞሪታኒያ የዜና ወኪል በዘገባው፣ ከሀገሪቱ በስተደቡብ ምዕራብ ከምትገኘው ንዲጎ ከተማ አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ "የሞሪታኒያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ሰኞ፣ ሰኔ 24 ቀን በአትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ ላይ በተገለበጠችው ባህላዊ የአሣ ማጥመጃ ጀልባ ላይ ተሳፍረው የነበሩ የ89 ሰዎችን አስክሬን አግኝተዋል" ብሏል።

በተጨማሪም የባህር ጠረፍ ጠባቂዎቹ አንዲት የአምስት አመት ሴት ልጅን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎችን ማትረፋቸውንም፣ ዘገባው አመልክቷል።

በህይወት የተረፉት ሰዎች ጀልባዋ ከሴኔጋል እና ጋምቢያ ድንበር ላይ 170 መንገደኞችን አሳፍራ መነሳቷን መናገራቸውን የጠቀሰው ዘገባ፣ 72 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁን ጠቅሷል። ማንነታቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ከፍተኛ ባለስልጣንም መረጃው ትክክል መሆኑን ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አረጋግጠዋል።

በኃይለኛ ሞገድ ምክንያት በአትላንቲክ ውቂያኖስ ላይ የሚደረግ ጉዞ እጅግ አደገኛ ሲሆን፣ ከመጠን በላይ ሰዎችን በጫኑ አቅም አልባ ጀልባዎች የሚጓዙት ስደተኞች አብዛኛውን ጊዜ የሚጠጡት በቂ ውሃ የላቸውም። ነገር ግን በሜዲትራንያን ባህር ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እየጨመረ በመምጣቱ፣ በውቂያኖሱ በኩል የሚጓዙ ፍልሰተኞች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

እ.አ.አ በ2023 በስፔን ካናሪ ደሰቶች ላይ ያረፉ ፍልሰተኞች ቁጥር በእጥፍ የጨመረ ሲሆን፣ በአንድ አመት ብቻ 39 ሺህ 910 ሰዎች መመዝገባቸውን የስፔን መንግሥት አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG