በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተወካዮች ምርጫ በዩናይትድ ስቴትስ


የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ ማክሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2003 ዓ.ም. እንደራሴዎቹን ይመርጣል፡፡

ማክሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2003 ዓ.ም. የዩናይትድ ስቴትስ ሕዝብ እንደራሴዎቹን ለተወካዮች ምክር ቤቱ ሙሉ በሙሉ እና ለሕግ መወሰኛው በከፊል፣ እንዲሁም ከግማሽ በላይ በሚሆኑት ስቴቶች ደግሞ አገረ ገዥዎቹን ይመርጣል፡፡


ሰሞኑን በጀመርነው በዚሁ የዩናይትድ ስቴትስ የአራት ዓመት አጋማሽ ምርጫ ዝግጅት የኔቫዳው ምርጫ ውድድር ላይ አተኩራ ትዝታ በላቸው ኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያንን አነጋግራለች፡፡

በኔቫዳው ምርጫ በሴኔቱ አብዝኃ ፓርቲ መሪ የሆኑት ሃሪ ሪድ እምብዛም ከማይታወቁት የቲ ፓርቲ እና የሌሎች በርካታ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ድጋፍ ያላቸው ሬፐብሊካኗ ሼረን አንግልስ ጋር ትንቅንቅ መያዝ ለኦባማ አስተዳደር እና ፖሊሲአቸው ብርቱ አንድምታ አለው ይባላል፡፡

በላስ ቬጋስ ከተማ የሚኖሩት አቶ ጌትነት ፀጋዬ፣ አቶ ስሜነህ መሸሻና ጋዜጠኛ ሣምሶን ውብሸትን አግኝታለች ትዝታ፡፡ “በዴሞክራቱ ሴናተር ሃሪ ሪድ እና በሬፐብሊካኗ ሼረን አንግልስ መካከል የሚካሄደው ውድድር የከረረ” ብለዋል አቶ ስሜነህ።

“ቲ ፓርቲ የተባለ የወግ አጥባቂዎች እንቅስቃሴ ተሣትፎ በዘንድሮው የፕሬዚዳንቱ የአራቱ ዓመታት አጋማሽ ምርጫ ላይ ከፍተኛ አንድምታ እንዳለው ቢነገርም የኔቫዳ ክፍለ ግዛት ኢትዮጵያዊያን በሁለቱ የምርጫው ተቀናቃኞች መካከል ዋናው አከራካሪ ነጥብ ኢኮኖሚውና የሥራ አጡ ቁጥር መብዛት ነው” ይላሉ አቶ ጌትነት ፀጋዬ፡፡

“ብሔራዊው የሥራ አጥ ቁጥር በ9 በመቶ ሲገመት የኔቫዳው የሥራ አጥ ቁጥር ከ14 ከመቶ በላይ ነው” ይላሉ፡፡ የሆነ ሆኖ የወግ አጥባቂዎች ውድድር የዘንድሮውን የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ለየት እንዳደረገው አቶ ስሜኔህ መሸሻ ይናገራሉ።

ሁለቱ የኔቫዳ የሴኔት እጩዎች ሴናተር ሃሪ ሪድና ሬፑሊካን ሼረን አንግልስ በጥቂት ነጥቦች ነው የሚቀዳዳሙት። ሴናተር ሪድ ቢሸነፉ ለፕሬዚደንት ኦባማ አስተዳደር አንድምታ እንደሚኖረው በላስ ቬጋስ የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሣምሶን ውብሼት ገልፆልናል።

አቶ ጌትነት ፀጋዬም ይስማማሉ።

የሼረን አንግልስ ወግ አጥባቂ የምርጫ ፖሊሲ ሶሻል ሴክዩሪቲ (የአሜሪካዊያን የጡረታ ዋስትና) በግል እንዲተዳደር፣ የዩናይትድ ስቴትስ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ ጥብቅ እንዲሆን፣ በተለይም አዲሱን የፕሬዚዳንት ኦባማ የጤና አገልግሎት መርኃግብር እንዲሠረዝ የሚያቀርቡት ሃሣብ አሳሳቢ መሆኑ ይነገራል፡፡ ጋዜጠኛ ሣምሶን “በተስፋና በፍርሃት መካከል ያለ ውድድር” ይለዋል።

በኔቫዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በምርጫው ለማሣተፍና ድምፃቸውን ለማግኘት እንቅስቃሴ መኖሩን አቶ ስሜነህ መሸሻ ገልፀውልናል።

ኔቫዳ ከምርጫው ዕለት በፊት ድምፅ በመስጠት ባላት ፖሊሲ እራሣቸው ቀድመው ድምፅ የሰጡት አቶ ጌትነት ፀጋዬ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም በምርጫው እንዲሣተፉ ያበረታታሉ።

ጋዜጠኛ ሣምሶን ከዘንድሮው የUS የአጋማሽ ዘመን ምርጫ “ብዙ የምንማረው አለ” ይላል።

የላስ ቬጋስ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን አቶ ስሜነህ መሸሻን፣ አቶ ጌትነት ፀጋዬን እንዲሁም ጋዜጠኛ ሣምሶን ውብሸትን እናመሠግናለን።

XS
SM
MD
LG