እስራኤል ምሽቱን በቤሩትና አካባቢዋ ተከታታይና ከፍተኛ የተባለ የአየር ጥቃት ፈፅማለች፡፡ የአየር ድብደባው በሌባኖስ እና በሶሪያ መካከል የሚገኝን የድንበር መተላለፊያ ላይ በመፈጸሙም፣ በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ከጥቃቱ መሸሽ እንዳይችሉ አድርጓል።
ከቤሩት ዳርቻ ባለ የመኖሪያ አካባቢ የተከሰተው ከፍተኛ ፍንዳታ፣ ጭስና ነበልባል በምሽቱ ሰማይ ላይ ሲያሳይ፣ ንዝረቱ በኪሎሜትሮች ርቀት ላይ በመዲናዋ በሚገኙ ሕንፃዎች ላይ ተሰምቷል።
ከቤሩት 48 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና በሌባኖስ እና ሶሪያ ድንበር ላይ ሐሙስ ሌሊቱን የተፈፀመው ድብደባ፣ የድንበር መተላለፊያው እንዲዘጋ አስገድዷል። በዚህም በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች የእስራኤልን ድብደባ መሸሽ እንዳይችሉ አድርጓል።
እስራኤል ድንበሩን ኢላማ ያደረገችው፣ ለሄዝቦላ የጦር መሣሪያዎች ማስተላለፊያነት በመዋሉ ነው ስትል ገልጻለች፡፡ ሄዝቦላ አብዛኛውን የጦር መሣሪያዎች ከኢራን በሶሪያ በኩል እንደሚያገኝ ይታመልናል ሲል የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
በእስራኤል እና በሄዝቦላ መካከል እየተካሄደ ባለው ውጊያ ሄዝቦላ ዛሬ ዓርብ 100 የሚሆኑ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፉን እስራኤል አስታውቃለች፡፡
መድረክ / ፎረም