በአውሮፓ፣ የመረጃ ጥበቃ ሕጉን በመተላለፉ፣ ከፍተኛ ቅጣት የተጣለበት የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ፣ በኬንያ ደግሞ፣ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛው ላይ የሚወጡ፣ የጥላቻ እና ሁከት ቀስቃሽ ይዘቶችን ይቆጣጠሩ የነበሩ የቀድሞ ሠራተኞቹ ክሥ መሥርተውበታል።
ካለፈው ዓመት ግንቦት ወዲህ፣ በሜታ እና መሠረቱ ካሊፎርኒያ በኾነው ሳማ የተባለ ኩባንያ ላይ፣ ሦስት ክሦች ተመሥርተዋል። ሳማ፣ ፌስ ቡክ ላይ የሚወጡ የጥላቻ እና ሁከት ቀስቃሽ ይዘቶችን እንዲቆጣጠር ተቀጥሮ የነበረ ኩባንያ ነው።
ሳማ እና የፌስቡክ፣ የዋአትስአፕ እንዲሁም የኢንስታግራም ባለቤት የኾነው ሜታ፣ በክሡ ጭብጥ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በኤኤፍፒ ቢጠየቁም፣ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
ሁለቱን ክሦች በሳማ ላይ የመሠረቱት፣ የቀድሞ ሠራተኞቹ ናቸው፡፡ ከእነርሱም፣ ዳንኤል ሙታንግ የተባለው ሠራተኛ ያቀረበው ክሥ፥ ኢሰብአዊ የሥራ ኹኔታ፣ የተጭበረበረ የአቀጣጠር ዘዴ፣ በቂ ክፍያ ባለመስጠት እና በሰዓቱ ባለመክፈል፣ እንዲሁም ለአእምሮ ጤና ድጋፍ አለመኖር የሚሉት ይገኙበታል። የሠራተኛ ኅብረት ለመመሥረት በመሞከሩም ከሥራው እንደተባረረ ዳንኤል ገልጿል።
ባለፈው መጋቢት፣ ሳማ ኩባንያ የናይሮቢ ቢሮውን ሲዘጋ፣ 184 ሠራተኞች ያለአግባብ እንደተባረሩ በመጥቀስ ክሥ መሥርተዋል።
ባለፈው ታኅሣሥ፣ በፌስቡክ በተሠራጨ የጥላቻ መልዕክት ምክንያት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ በሚል፣ ሜታ ኩባንያ፥ ለሰለባዎች ካሳ የሚውል የ1ነጥብ6 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ እንዲያቋቁም ታዝዞ እንደነበር ይታወሳል።