በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሜሲ 8ኛውን ባሎንዶር በማሸነፍ የራሱን ክብረ ወሰን ከፍ አደረገ


የ36 ዓመቱ አርጀንቲናዊ የእግር ኳስ ጠቢብ ሜሲ ሽልማቱን ሲቀበል ፓሪስ እአአ ጥቅምት 30/2023
የ36 ዓመቱ አርጀንቲናዊ የእግር ኳስ ጠቢብ ሜሲ ሽልማቱን ሲቀበል ፓሪስ እአአ ጥቅምት 30/2023

- በሴቶች ስፔናዊቷ ቦንማቲ የባሎንዶር አሸናፊ ኾናለች

ባለፈው ዓመት የዓለም ዋንጫን በማንሣት የሕይወት ሕልሙን እውን ያደረገው ሊዮኔል ሜሲ፣ አሁን ደግሞ ስምንተኛውን ባሎንዶር በማሸነፍ የዓለም ምርጥ ተጨዋችነቱን አስመስክሯል፡፡

የ36 ዓመቱ አርጀንቲናዊ የእግር ኳስ ጠቢብ ሜሲ፣ የማንቸስተር ሲቲውን የፊት መሥመር ተጫዋች ኤርሊንግ ሃላንድንና የቀድሞ የፒኤስጂ ቡድን ጓደኛውን ኪሊያን ምባፔን በማስከተል የባሎንዶር ክብሩን ተጎናጽፏል፡፡

ሜሲ፣ ትላንት ሰኞ ምሽት፣ ሽልማቱን በፓሪስ ከተቀበለ በኋላ፣ ለዚኽ ክብር አብቅተውኛል ያላቸውን የአርጀንቲናውን አሠልጣኝ፣ የቡድን አጋሮቹንና ሌሎች ሠራተኞችን አመስግኗል።

"ዛሬ ማታ በደስታ ውስጥ ነኝ። መቼም የማይተወኝ ደስታ ነው፤ ለብዙ ዓመታት እንደሚዘልቅ ተስፋ አደርጋለኹ፤”ሲል፣ ሜሲ በአስተርጓሚ ተናግሯል። “ጉድለታችን የዓለም ሻምፒዮን መኾን ነበር። አርጀንቲና የዓለም ሻምፒዮን እንድትኾን የረዱትን ኹሉ ላመሰግን እወዳለኹ፤” ሲልም አክሏል።

“ይህን ሽልማት እና ዋንጫ፣ ከአንተ እና ከመላው የአርጀንቲና ጓዶቻችን ጋራ እጋራለኹ፤” በማለት፣ ሜሲ እ.ኤ.አ. በ1986 አርጀንቲና የዓለም ዋንጫን ስታሸንፍ ቁልፍ ሚና ለነበረው ዲያጎ ማራዶናም ክብር ሰጥቷል።

የቀድሞው የባርሴሎና እና ፓሪስ ሴንት ዠርሜን አጥቂ መሲ፣ ወደ ዩናይትድ ስቴትሱ ኢንተር ሚያሚ ከተዛወረ በኋላ፣ ከቡድኑ ጋራ የመጀመሪያውን የዩናይትድ ስቴትስ ሊግ ዋንጫ አንሥቷል።

የዩናይትድ ስቴትስ ሜጀር ሊግ ተጫዋች፣ የባሎንዶር ሽልማትን ሲያሸንፍ የሜሲ የመጀመሪያው ነው።

ስምንት ባሎንዶሮችን ካሸነፈው ሜሲ በመቀጠል ከፍተኛ የባሎንዶር ሽልማት ያሸነፈው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው፡፡ ሮናልዶ አምስት ጊዜ ያሸነፈ ሲኾን፣ ሚሼል ፕላቲኒ፣ ዮሃን ክራይፍ እና ማርኮ ቫን ባስተን እያንዳንዳቸቸው ሦስት ጊዜ አሸንፈዋል።

በ35 የሊግ ጨዋታዎች 36 ጎሎችን በማስቆጠር ክብረ ወሰን የያዘው ሲቲ፣ የሦስትዮሽ ዋንጫን ማለትም ፕሪሚየር ሊግን፣ ሻምፒዮንስ ሊግንና ኤፍኤ ካፕን ሲያነሣ በማሸነፍ፣ በኹሉም ውድድሮች 52 ግቦችን ያስቆጠረው የኖርዌዩ ኢንተርናሽናል ሃላንድ፣ በምርጥ ግብ አስቆጣሪነት፣ የገርድ ሙለር ሽልማት ተበርክቶለታል።

ከዓመቱ ምርጥ 10 ተጫዋቾች ውስጥ፣ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ሃላንድን ጨምሮ አምስቱ፣ የማንችስተር ሲቲ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በሴቶች የዓለም ዋንጫ፣ ስፔንን ለድል ያበቃችው አይታና ቦንማቲ ደግሞ፣ የሴቶችን የባሎንዶር ሽልማት አሸንፋለች። ተጫዋቿ ባርሴሎና የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ እና የስፔን ሊግን እንዲያሸንፍም ቁልፍ ሚናዋን ተወጥታለች፡፡

በሌሎች ሽልማቶች፣ አርጀንቲናዊው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ እና የአስቶንቪላ ግብ ጠባቂ ኤሚሊያኖ ማርቲኔዝ፣ የዓለም ምርጥ ግብ ጠባቂ በመኾን አሸንፏል።

ማንችስተር ሲቲ፣ የዓመቱ ምርጥ የወንዶች ክለብ፣ ባርሴሎና ደግሞ ምርጥ የሴቶች ክለብ ተብለዋል፡፡ የሪያል ማድሪዱ ጁድ ቤሊንግሃም፣ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ኾኖ ሲሸለም፣ የክለብ አጋሩ ቪኒሺየስ ጁኒየር ደግሞ፣ ዘረኝነትን ለመዋጋት ባደረገው ጥረት እውቅና አግኝቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG