በዚህ ዙሪያ በግንባሩ የሥራ አስፈጻሚ ኰሚቴ አባል ከሆኑት ከዶክተር መረራ ጉዲና ጋር ቪኦኤ ባደረገው ውይይት "በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ አስተዳደር ለመለወጥ ስብስባችሁን ወደ ግንባር ማሸጋገር የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ይረዳል ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው?" ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡
ዶ/ር መረራ "ተባብራችሁ አንድ ውጤት አምጡ" የሚል ጥያቄ፤ "ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ" የሚል ብሶት በተደጋጋሚ ሲቀርብላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች የተሻለ ቅንጅት፣ የተሻለ ሕብረት፣ የተሻለ መቀራረብ ፈጥረው ሕዝቡ የሚፈልገውን መስጠት ደረጃ ላይ ለመድረስ ሣይችሉ መቆየታቸውን ዶ/ር መረራ ገልፀው ይህንን የሕዝብ ጥሪ ተቀብሎ በተሻለ ሁኔታ የማስተባበር፣ አመራር የመስጠት፣ ሥራ ላይ የመሠማራት፣ የተግባር ኮሚቴዎች የተሻለ እንዲንቀሣቀሱ የማድረግ፣ በተለይም ቢሮዎችን በጋራ የመክፈትና በጋራ የማንቀሣቀስ ሥራዎችን ለማከናወን መወሰናቸውን አመልክተዋል፡፡
እርዳታ ሲሰጥም "እናንተ ስድስት፣ ሰባት፣ አሥር ናችሁ፤ የኛ ጉዳይ ግን አንድ ነው" የሚል ስሞታም ከደጋፊዎቻቸው ያጋጥማቸው እንደነበር የጠቆሙት ዶ/ር መረራ ግንባርን በተሻለ መንገድ በግንባር ለመግጠም ያመቻል የሚል እምነት እንዳላቸውና ይህንንም ደጋፊዎቻቸው የተቀበሉት እንደሚመስል ተናግረዋል፡፡
"በእናንተ በራሣችሁ፣ በስድስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያሉ ድርጅቶች የርዕዮተ-ዓለም ልዩነቶቻችሁን እንዴትና በምን መንገድ አቻችላችሁ ነው ግንባር መፍጠር የምትችሉት?" የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
ሰሎሞን ክፍሌ ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ያዳምጡ።