የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ትላንት በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርተዋል፡፡
የሃገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች ያነሷቸው ጥያቄዎች ከምርጫው ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ካለፉት ምርጫዎች ሁሉ በተለየ ሁኔታ ገዥው ፓርቲ ከሁለት መቀመጫዎች በስተቀር የፓርላማውን መቀመጫዎች ጠቅልሎ መውሰዱ "በሃገሪቱ የፖለቲካ ሂደትና በብዙኅነት አቅጣጫ ላይ አደጋ የለውም ወይ?" የሚል ነበር፡፡ እንዲያውም በቻይና እንደሚታየው ዓይነት የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ሊፈጠር እንደሚችልም ተመላክቷል - በጥያቄዎቹ፡፡ ይህንን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም ሲሉት ነበረ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በዚህ ፈፅሞ አይስማሙም፡፡ እንዲህ አሉ፡-
"በኢትዮጵያ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ሊፈጠር የሚችልበት ሁኔታ ፈፅሞ የለም፡፡ በሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ መኖር ምክንያት ይህ በምንም ዓይነት ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ ምናልባት እንደስዊድን ያለ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ወይም እንደጃፓኑ ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተፅዕኖ የሠፈነበት ሥርዓት ለአንድ አሠርት ዓመት ወይም ወደዚያ የሚጠጋ ጊዜ ሊኖር ይችላል፡፡ ግን በምንም ዓይነት በኢትዮጵያ የአንድ ፓርቱ ሥርዓት ሊፈጠር አይችልም፡፡"
የዘንድሮው ምርጫ ውጤት በሠላማዊና ሕጋዊ መንገድ በሃገሪቱ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ኃይሎችን የሚያዳክምና ፅንፈኛ ለሚባሉ የፖለቲካ ኃይሎች አመቺ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል የሚለውን ክርክርም አቶ መለስ ዜናዊ ጨርሶ አይቀበሉትም፡፡ እንዲያውም ፓርቲያቸውም ሆነ የሚመሩት መንግሥት የሚከተሏቸው ፖሊሲዎች ፅንፈኛ የሚባሉ ኃይሎችን እንኳ እያለዘበ ወደ ሕጋዊና ሠላማዊ የፖለቲካ መስመር እያስገባ መሆኑን በመግለፅ ይከራከራሉ፡፡ እንደምሣሌም ከጥቂት ወራት በፊት ከመንግሥት ጋር የተፈራረመውን የምዕራብ ሶማሌ ነፃነት ግንባርና በቅርብ ጊዜ ደግሞ ተመሣሣይ ስምምነት ሊፈርም ነው ያሉትን የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር አንድ አንጃም ይጠቅሣሉ፡፡
የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ግንቦት 18 ቀን 2002 ዓ.ም ካወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀበሉት የተዘረዘሩትን "ጥሬ ሃቆች" ያሏቸውን ብቻ ነው፡፡ በእነርሱም ላይ እንኳ አንዳንድ የተዛቡ ነገሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ መደምደሚያውን በተመለከተ ያላቸውን ቅሬታ ግን አልሸሸጉም፡፡
"ከሞላ ጎደል በትክክል አስቀምጠውታል፤ ድምዳሜውን ከፖለቲካ ዓላማቸው ጋር አብሮ በሚሄድ ልክ ሰፍተው አስቀምጠውታል፡፡ የፖለቲካ ድምዳሜውን ለራሣቸው ዓላማ በሚመጥን መልኩ የሰፉት ስለሆነ እኛ ልንለብሰው አንችልም፡፡ ጥሬ ሃቁ ግን ጥሬ ሃቅ ስለሆነ ልንቀበለው የምንችል ነው፡፡" ብለዋል፡፡
የምርጫውን ውጤት ተከትሎ አስተያየቱን የሰጠው የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢ ቡድን ብቻ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው ከሚባሉት መንግሥታት መካከል የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትም አስተያየቱንና ውጤቱ ያሣሰበው መሆኑን ገልጿል፡፡ ደግሞም የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሰብዓዊ እርዳታ በሰፊው ይለግሣል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን እንዴት እንደሚመለከቱትም ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ሃገሪቱ ያላት ግንኙነት በሁለቱም ሃገሮች የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑን አበክረው ያስረዱት አቶ መለስ ይህ መልካም ግንኙነት ወደፊትም እንዲቀጥል እንደሚፈልጉ አረጋግጠዋል፡፡ "ግን - አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ - ኢትዮጵያ በሞግዚት የምትተዳደር ሃገር አይደለችም፡፡ ዩናይትድ ስቴትስም በዚህ ረገድ አንድ ጥርጣሬ የላትም፡፡" የምርጫው ውጤት ይህንን የሚያስቀይር ከሆነ ግን፤ ይቀጥላሉ አቶ መለስ፡-
"ዩናይትድ ስቴትስ የታክስ ከፋዮቿን ገንዘብ ይሆናል እርሷ ባሻት ሁኔታ ልትጠቀምበት ሙሉ መብቷ ነው፡፡ የምርጫው ውጤት ትብብራችንን ለመቀጠል የሚያስችል አይደለም ብለው የሚያስቡ ከሆነ - መልካም፤ እስከዛሬ ላደረጉልን እርዳታ እያመሠገንን ወደፊት መቀጠል ነው፡፡ ይሁንና ' ከዚህ ወይም ከዚያ ሃገር የሚመጣው የእርዳታ እህል ከቆመ የኢትዮጵያ ሕዝብ በረሃብ ያልቃል' ብለው የሚያስቡ ሰዎች ካሉ ይህቺ ሃገር እንደት እንደምትተዳደር ምንም የማያውቁ ናቸው፡፡"
ረቡዕ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ አልነበሩም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፣ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖን መግለጫዎችን ሰጥተዋል፡፡ ሁሉም በምርጫው ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡
ከአፍሪካ ሕብረት ታዛቢዎች በስተቀር የተቃዋሚዎቹና የመንግሥት ባለሥልጣናቱ መግለጫዎች ቢያንስ መንፈሣቸው የሚጣጣም አይደለም፡፡ ይህ አለመጣጣም እንዲረግብ የማንም ጤናማ ሰው ምኞት ነው፡፡ ታሪክ ግን በምኞት አይሠራም፡፡
መለስካቸው አምሃ - ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ከአዲስ አበባ፡፡