ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአምስት ዓመትየኢኮኖሚ እቅዳቸውን ይፋ አድርገዋል። አገሪቱን ለመጭዎቹ አምስት ዓመታት የሚያስተዳድረው የኢህአዴግ መንግስት በጥቅምት ወር የሚመሰርተው አዲስ መንግስት በርካታ ስራዎች ይጠብቁታል።
አገሪቱ ከውጭ የምግብ እርዳታ ነፃ እንድትወጣና ኢኮኖሚው በአማካይ በዓመት ከ11-14 ከመቶ እንዲያድግ እቅድ ወጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኢኮኖሚ እቅዱን ገቢራዊነት አስመልክተው ሲናገሩ በ10 ከመቶ እናድጋለን ስንል እንደ እብድ ታይተን ነበር፣ እኛ ግን ከዚያም በላይ አሳክተናል ይላሉ።
“የዛሬ አምስት ዓመትየ10ከመቶ እድገትን የበላይ ድካችን እንደሆነ ስናስታውቅ፤ እብደት ነው ተብለን ነበር፤ ባይሆን በ7 ከመቶ ለማደግ ስናቅድ በአጋሮቻችን ዘንድ ይሄ የህልም እንጀራ መግመጥ ነው ተብለን ነበር” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ።
ውጤቱ ለኢትዮጵያ ከታቀደው በላይ የሰባት ዓመትአማካይ የ11.1 ከመቶ እድገት ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይናገራሉ። በመጭው አምስት አመታት ከኢኮኖሚ እድገቱ በተጓዳኝ የአገር ጠቅላላ ምርት GDP በእጥፍ ለመጨመር የአምስት አመቱ መርኃ ግብር ግቡን አስቀምጧል።
አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና ተቋማት ግን የኢትዮጵያን የ5ዓመትእቅድ ብቻ ሳይሆን በጥርጣሬ “የህልም እንጀራ ነው” የሚሉት ባለፉት ሰባት ዓመታት ተመዘገቡ የሚባሉትን እድገቶችም ጭምር ነው።
ባለፈው ሳምንት የኦክስፈርድ ዩኒቨርስቲ የድህነትና የሰብአዊ ልማት ተቋም ኢትዮጵያን ከ104 በማደግ ላይ ካሉ አገሮች የጠቅላላ የድህነት መለኪያ መስፈርት ከመጨረሻ ሁለተኛ አድርጓታል። በዚህ መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ የምትሻለው ከኒዠር ብቻ ነው። ጎረቤት ኬንያና ጅቡቲ በርቀት ተሽለው ሲገኙ፤ ሶማሊያ በቅርበት ከኢትዮጵያ የተሻለ የድህነት መለኪያ አስመዝግባለች።
የሄ MPI (Multidimentional Poverty Index) የሚባለው መለኪያ የድህነት መጠንን በሰንጠረዥ የሚያሰፍረው ዜጎች በትምህርት፣ በጤናና በኑሮ ደረጃ ያላቸውን ሁኔታ ገምግሞ ነው።
ለኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የብድር አገልግሎት የሚሰጠው የአፍሪካ ልማት ባንክ ድህነት ቅነሳናና የኢኮኖሚ እድገት በትይዩ መስመር እኩል የሚጓዙ ስሌቶች አይደሉም ይላል።
ከወራት በፊት ለቪኦኤ በተለይ መግለጫ የሰጡት የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት ዶናልድ ካቢሩካ የኢኮኖሚ እድገት የዜጎችን ኑሮ ለመለወጥና ድህነትን በአንድ አገር ውስጥ ለመቀነስ የ10 ከመቶው እድገት ለረጅም ዓመታት መቀጠል አለበት ብለዋል።